አፍሪካ ከዓለም የኮቪድ 19 ክትባት ሽፋን ወደ ኋላ ቀርታለች

Your browser doesn’t support HTML5

አፍሪካ ከዓለም የኮቪድ 19 ክትባት ሽፋን ወደ ኋላ ቀርታለች

የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ የኮቪድ 19 ከትባት ሽፋን ምንም ለውጥ ባለማሳየቱ፣ 1.2 ቢሊዮን የሚሆነውን የአህጉሩን ህዝብ፣ በየጊዜው እየጨመረ ለመጣው ቫይረስ በከፍተኛ ደረጃ አጋልጦታል ሲል አስጠንቅቋል፡፡

ከዓለም ጤና ድርጅት የተገኙ አዳዲስ ቁጥሮች በሀምሌ እና መስከረም ወር በሽታን የመከላከል አቅም ከግማሽ በላይ ማሽቆልቆሉንና የአዳዲስ ተከታቢዎች መጠንም በከፍተኛ ደረጃ መቀነሳቸውን ያመለክታሉ፡፡

በዚህ አካሄድ የሚቀጥል ከሆነ፣ አብዛኞቹ የአፍሪካ አገሮች በዓመቱ መጨረሻ 70 ከመቶ የሚሆነው ህዝቦቻቸውን ለማስከተብ የተቀመጠውን ዓለም አቀፍ ግብ ላያሟሉ ይችሏሉ ሲሉ የዓለም ጤና ድርጅት ባለሥልጣናት ይናገራሉ፡፡

ምንም እንኳ ይህ መሰናክል ቢኖርም ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑትን የህብረተሰብ ክፍሎች፣ በተለይም አረጋውያንን በማስከተብ ረገድ መጠነኛ መሻሻል መደረጉን፣ የዓለም ጤናድርጅት አስታውቋል፡፡

በሌላ መልካም ዜናም፣ ባላፉት 12 ሳምንታት ወረርሽኙ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ አፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ አነስተኛ የኮቪድ ተጋላጮችን ቁጥር ያስመዘገበች ሲሆን፣ የሟቾች ቁጥርም በመላው አፍሪካ ዝቅተኛ መሆኑን ድርጅቱ ጨምሮ አመልክቷል፡፡

በአፍሪካ የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ማትሺድሶ ሞኤቲ ሲያብራሩ “የክትባት አቅርቦቱ አሁን ችግር እንደሌለበት መገንዘቡ አስፈላጊ ነው፣ ካላፈው ዓመት መገባደጃ ጋር ሲነጻጸር፣ አገሮች አሁን በየ100 ሰዎች የሚያገኙት የክትባት መድሃኒት መጠን በእጥፍ ጨምሯል፡፡

እንዳለመታደል ሆኖ ክትባቶች ከባድ የኮቪድ 19 በሽታን ፣ ሆስፒታል መግባትንና የሞትን መጠን ለመቀነስ የረዱ ቢሆንም፣ ሰዎችን ግን ፍርሃታቸው እየቀነሰ፣ ክትባቶችንም ለመውስደ ፈቃደኝነታቸው እያነሰ ነው፡፡” ብለዋል፡

በርካታ የአፍሪካ አገሮች በክትባት ጥሩ ውጤት ማስመዘገባቸውን የገለጸው የዓለም ጤና ድርጅት፣ በቅርቡ የተቀላቀለቻቸው ላይቤሪያን ጨምሮ፣ ሞሪሸስና ሲሸልስ በአማካይ 70 ከመቶ በላይ መድረሳቸውን ገልጿል፡፡

ሩዋንዳም በቅርብ ጊዜ ውስጥ ከእነዚህ አገሮች ጋር እንደምትቀላቀልም የጤና ድርጅቱ አስታውቋል፡፡

በምህጻረቃሉ GAVI የተባለው ክትባቶችን ለማዳረስ የሚሰራው ህብረት ልዩ አማካሪ የሆኑት ኦሬሊያ ንጉዬን፣ ድርጅታቸው እስካሁን ለአፍሪካ 670 ሚሊዮን የክትባት መድሃኒቶችን ማከፋፈሉን አስታውቀዋል፡፡

ወረረሽኙ እስካለና ስጋት መፍጠሩን እስከቀጠለ ድረስ፣ ክትባቶችን ወደ አፍሪካ መላኩ እንደሚቀጥልም ንጉዬን ተናግረዋል፡