አፍጋኒስታን፤ የአሜሪካ አጋሮች ስጋትና የመውጣት ጥድፊያ

አፍጋኒስታን ውስጥ ከጀመርኖች ጋር ሲሰሩ የነበሩ የአፍጋን ዜጎች በካቡል ኤርፖርት፣ የጀርመን አውሮፕላን ውስጥ፣ እኤአ ነሀሴ 17 2021

የዩናይትድ ስቴትስ ጦሯን ከአፍጋኒስታን ማውጣትና የአፍጋኒስታን መንግሥትን መውደቅ ተከትሎ፣ የአሜሪካ አጋር የሆኑ የኔቶ አባል አገሮች ዜጎቻቸውን ከአፍጋኒስታን ለማውጣት እየተጣደፉ ነው፡፡ ብዙዎቹ የአውሮፓ ባለሥልጣናት፣ የታሊባን አገሪቱን መቆጣጠር፣ የሽብርተኝነት መስፋፋት አደጋን፣ እንዲሁም የስደተኞች ጎርፍ እንደገና መከሰት ምክንያትን ሊሆን ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

ብሪታኒያ እና ሌሎቹ የኔቶ አጋር አገሮች አብረዋቸው ሲሰሩ የነበሩ የአፍጋኒስታን ዜጎችን ጨምሮ ባላፈው እሁድ ዜጎቻቸውን ከአፍጋኒስታን አውጥተዋል፡፡

የኔቶ አባል አገሮች፣ እኤአ አፍጋኒስታንን በመውረር አብረው የተሰለፉት እኤአ በ2001 ነበር፡፡ ኔቶ የዓለም አቀፉን ደህንነት አጋዥ ኃያል ኃላፊነት የተረከበው፣ ከሁለት ዓመት በኋላ ነበር፡፡ ህይወታቸውን ካጡት አሜሪካውያን በተጨማሪ፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ የኔቶ ወታደሮችም፣ በሁለት አስርት ዓመታቱ ግጭት ውስጥ ተገድለዋል፡፡

ትናንት ማክሰኞ፣ በተካሄደው ጋዜጣዊ መግለጫቸው፣ የኔቶ ዋና ጸሀፊ፣ ለአፍጋኒስታን በታሊባን እጅ መውደቅ፣ የአፍጋኒስታንን የፖለቲካ መሪዎችን ተጠያቂ አድርገዋል፡፡

“የአፍጋን የፖለቲካ መሪዎች የአፍጋኒስታን ዜጎች አጥበቀው ለሚፈግሉት ሰላማዊ መፍትሄ ታሊባኖችን ሊያስቆሙ አልቻሉም፡፡

በኢሰክስ ዩኒቨርስቲ፣ የውጭ ፖሊሲ ተመራማሪ የሆኑት፣ ነታሻ ሊንድስቴድ፣ ያንን ሰላማዊ መፍትሄ ማምጣት አለመቻል ለኔቶ ትልቅ ትርጉም ይኖረዋል ይላሉ

“እንደሚመስለኝ ኔቶ ከትልቅ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ይልቅ ሰላማዊ ሁኔታዎች ተጠብቀው እንዲቀጥሉ መከላከል በሚያስችሉ ውስን ግቦች ላይ ብቻ የሚያተኩር ይመስለኛል፡፡”

የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ ለአፍጋኒስታን መንግስት መውደቅ፣ የቀድሞ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕን፣ ተጠያቂ አድርገዋል

“ግንኙነቱ የተደረገው ቀጥታ ከታሊባኖች ጋር ነው፡፡ የአፍጋንን መንግሥት የጨመረ አልነበረም፡፡ ያ ደግሞ በወቅቱ የነበረውን መንግሥት ችላ በማለት ክፉኛ ጎድቶታል፡፡ አጋር የሆን ዓለም አቀፍ አገሮችም ሁኔታው ደስተኞች አልነበርም ምክንያቱም የተሰማራነው በዩናይትድ ስቴትስ ማዕቀፍ ውስጥ ነው፡፡ ያንን ማዕቀፍ ሲያጥፉ እኛም መውጣት ነበረብን፡፡”

Your browser doesn’t support HTML5

አፍጋኒስታን፤ የአሜሪካ አጋሮች ስጋትና የመውጣት ጥድፊያ


ይሁን እንጂ፣ ብዙዎቹ ተንታኞች ደግሞ፣ ዩናይትድ ስቴትስ አወጣጡን የፈጸመችበትን መንገድ ተችተዋል፡፡

አሁንም የፖለቲካ ተንታኟ ነታሻ እንዲህ ይላሉ

“ሁሉ ነገር የጥድፊያ ነበር፡፡ የተቀናጀ አልነበረም፡፡ ከኔቶ አጋር አገሮች ጋር፣ ከፕሬዚደንት ባይደንም ሆነ ከእሳቸው አስተዳደር ጋር ብዙም የተደረገ ምክክር አልነበረም፡፡”

የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን፣ የአፍጋኒስታን መንግሥት መውደቅ፣ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ላይ የሚያስከተለው ትልቅ ተጽእኖ ይኖረዋል ብለዋል

“ከትርምሱ ማትረፍ የፈለጉ አሸባሪ ቡድኖች በአፍጋኒስታን ብቅ እያሉ ነው፡፡

ተንታኞች “ያ ስጋት ከአካባቢው ቀጠና ውጭ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ፣ በሚደረግ የጸረ ሽብርተኝነት ትግልም ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ አለው” ይላሉ፡፡

ከደቡብ ራጃራትናም፣ ዓለም አቀፍ ጥናትና ምርምር፣ ራፊዬሎ ፐንቱቺ እንዲህ ይላሉ

“ያለምንም ጥርጥር በመላው ዓለም ባሉ፣ የጅሃድ ቡድኖች ዘንድ የድል ስሜት መሰማቱ አይቀርም፡፡ ‘ተመልከቱ ድል ማድረግ የሚቻል ነገር ነው፡፡ ይህ ተስፋ የሌለው ትግል አይደለም፡፡ ስለዚህ ፍልሚያውን ቀጥሉ በእምነታችሁም ጸንታችሁ ቁሙ፡፡ ከ20 ዓመት በኋላ ይህን ውጊያ ማሸነፍ ትችላለሁ፡፡” ስለዚህ ይህ ትርክት ለተወሰነ ጊዜ ወደፊት የሚያንቀሳቅሳቸው ይመስለኛል፡፡

የአውሮፓ መሪዎች፣ ከአፍጋኒስታን አዲስ የስደተኞች ጎርፍ ሊነሳ እንደሚችል ያስጠነቅቃሉ፡፡ የፖለቲካ ጥገኝነት የሚሹ፣ በብዙሺዎች የሚቆጠሩ የአፍጋን ዜጎች፣ ሌዝቦስ በተባለችው የግሪክ ደሴት ላይ ታግተው ይገኛሉ፡፡ በመጭው ሰኞ ታሊባንን በመቃወም የተቃውሞ ሰልፍ እንደሚያደርጉም ተመልክቷል፡፡

በሌስቦስ የሚገኙ የአፍጋን ስደተኛ ኤሊና እንዲህ ይላሉ

“አሁን ወጣቱን የአፍጋኒስታን ትውልድ ምንድነው የሚጠብቀው? ለህጻንትስ ? ለሴቶችስ መብት ቢሆን?... ሁሉም ነገር በታሊባን ተደምስሷል፡፡”

ምዕራባውያን አገሮች፣ አፍጋኒስታንን ለቀው ለመውጣት፣ በሚራኮቱበትና፣ ታሊባኖች አገሪቱን መልሰው እየተረከቡ ባሉበት በዚህ ሰዓት ፣ ጥያቄው አሁንም እንዳለ ነው፡፡

በሌላም በኩል፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኤጀንሲዎች፣ ሁሉም አገሮች በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ተሰደው፣ በሰብአዊው ቀውስ ውስጥ የሚገኙ፣ የአፍጋኒስታን ዜጎችን ጉዳይ፣ ችላ እንዳይሉት እያሳሰቡ ነው፡፡ ይልቁንም፣ የደህንነት ጥበቃ እንዲደረግላቸውና የፖለቲካ ጥገኝነት ለሚሹት እንዲታይላቸው አሳስበዋል፡፡

በደረሰው ቀውስ፣ በዚህ ዓመት፣ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የአፍጋኒስታን ዜጎች፣ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ፣ አገር ጥለው መውጣት የቻሉት ጥቂቶች ብቻ ናቸው፡፡ የዩ.ኤን.ኤች.ሲ.አር ቃል አቀባይ፣ ሻቢያ ማንቱ፣ እንደሚሉት ለህይወታቸው የፈሩት አፍጋኖች፣ ምናልባት አገራቸውን ትተው ለመሄድ ስለወሰኑ፣ ለደህንነታቸው ዓለም አቀፍ ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል፡፡

እየተባባሰ በመጣው ቀውስ ሳቢያም፣ አጎራባች አገሮች፣ ለአፍጋኖቹ ድንበሮቻቸውን ክፍት እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡

አንዳንድ አገሮች ለህይወታቸው ሰግተው የፖለቲካ ጥገኝነት የሚጠይቁትን ማንገላታትና ለደህንነታቸው አስጊ ወደ ሆነው አገራቸው እንዲመለሱ እንዳያስገድዷቸውም የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብት ድርጅት ጠይቋል፡፡

አንዳንድ ታዛቢዎችም፣ የታሊባን ኃይሎች ሰሞኑን በመስጠት ላይ የሚገኙት መግለጫ ተስፋ ሰጭ ነው ይላሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የቀድሞ የአፍጋኒስታንን መንግስት ያገለገሉት እንደማይነኩ፣ የሴቶች በሥራ ገበታ ላይ የመሠማራትና የልጃገረዶች ወደ ትምህር ቤት የመሄድ መብት የተጠበቀ መሆኑን በታሊባኖች መገለጹ ተመልክቷል፡፡ ታሊባኖቹ ሁሉም “በእስልምና ህጉ መሠረት የሚፈጸሙ” ናቸው፡ ብለዋል፡”፡

ተጨማሪው ዘገባ የቪኦኤ ዘጋቢ ኸንሪ ሪጅዌል ከለንደን ከላከው የተወሰደ፡፡