ሰሜናዊ አፍጋኒስታን ውስጥ በተካሄደ የተለያየ ውጊያ ታሊባን እስከ አርባ ያህል የመንግሥት ወታደሮችን መግደሉ ተገለፀ።
ዋሺንግተን ዲሲ —
ጥቃቱ የደረሰው፣ ለአፍጋኒስታኑ ጦርነት ፖለቲካዊ መፍትሔ ለመሻት ሞስኮ ውስጥ ውይይት እየተካሄደ ባለበት ወቅት መሆኑ ነው። በክፍለ ሀገሩ ዋና ከተማ ኩንዱዘ አቅራቢያ ነው፣ ውጊያው ዛሬ ማክሰኞ የተካሄደው።
የክፍለ ሀገሩ ምክር ቤት ምክትል ሊቀ መንበር ሳፊላሀ አሚር ለአፍጋን መገናኛ ብዙኃን በሰጡት ቃል፣ በጥቃቱ ሃያ አምስት ወታደሮችና ሦስት ፖሊሶች መገደላቸውንና ሌሎች ሃያ የሚሆኑ መቁሰላቸውን ተናግረዋል።
ውጊያው ለሁለት ሰዓታት የዘለቀ ሲሆን፣ የታሊባን ቃል አቀባይ ዛቢሁላሀ ሙጃሂድ በሰጡት ማረጋገጫም፣ በጥቃቱ ሰላሳ የአፍጋኒስታን ብሔራዊ ጦር አባላት እንደተገሉ ነው የገለፁት።