የኢትዮጵያ ቢሮ ባልደረቦች የሆኑ ሁለት ሠራተኞቹ በህግ አስከባሪዎች መያዛቸውንና መደብደባቸውን የአፍሪካ ልማት ባንክ ማስታወቁን ሮይተርስ ዘገበ።
አድራጎቱ “ዲፕሎማሲያዊ አሠራርን በብርቱ የጣሰ” ሲል አውግዞታል።
ሠራተኞቹ ማክሰኞ፤ ጥቅምት 20/2016 ዓ.ም. በፀጥታ አካላት “ህገ ወጥ” ባለው መንገድ ከተያዙ በኋላ አካላዊ ጥቃት እንደተፈፀመባቸውና ለብዙ ሰዓታት ታስረው ከቆዩ በኋላ ያለአንዳች ማብራሪያ መለቀቃቸውን የልማት ባንኩ አመልክቷል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ለባንኩ የማፅናኛ መልዕክት ማስተላለፉንና የተፋጠነ ምርመራ እንደሚያደርግ ቃል መግባቱን ባንኩን የጠቀሰው የሮይተርስ ዘገባ ጠቁሞ የባንኩ እንቅስቃሴ በተፈጠረው አጋጣሚ አለመስተጓጎሉን ማስታወቁን ገልጿል።
ጉዳዩ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ዘንድ ከደረሰ በኋላ ለእንግልት የተዳረጉት የባንኩ ሠራተኞች መለቀቃቸውን የገለፀው የአፍሪካ ልማት ባንክ ከባለስልጣናቱ ጋር “በዲፕሎማሲያዊ መንገዶች” እየተነጋገረ መሆኑን አስረድቷል።
“መንግሥት ቅሬታችንን እንደተገነዘበ በይፋ አሳውቆ የድርጊቱን ክብደት እንደሚረዳና ሕግ የተላለፉ በሙሉ ጥብቅ ምርመራ እንደሚደረግባቸው አረጋግጦልናል" ከማለት ውጭ ቃል አቀባዩ ስለሁኔታው ተፈጥሮና ይዘት ዝርዝር ማብራሪያ ለመስጠት ፍቃደኛ አለመሆኑን ሮይተርስ አመልክቷል።
የአፍሪካ ልማት ባንክ ኢትዮጵያ ውስጥ የ308 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸው ስምንት ፕሮጀክቶች እንዳሉት ሮይተርስ የባንኩ ዌብ ሳይት ላይ የሠፈረን መረጃ ጠቅሷል።