“ኢህአዴግ የሠላማዊ ትግሉን መስክ እያጠበበ መንቀሳቀስ ወደማይቻልበት ደረጃ ላይ አድርሶናል” ሲል ገዥውን ፓርቲ ከስሷል።
መኢአድ ማክሰኞ፤ ጥር 29 / 2004 ዓ.ም ይፋ ያደረገው መግለጫው ገዥውን ፓርቲ ኢሕአዴግን በሰብዓዊና በዴሞክራሲያዊ መብቶች ጥሰት ይከስሣል፡፡
በተለይም የተቃዋሚ ፓርቲዎች አባላትን በማሠር፣ በመግደል፣ በመደብደብ፣ አካለ ጎደሎ በማድረግና በማዋከብ፣ እንዲሁም ከሥራና ከመኖሪያ ቀዬ ይወነድለዋል፡፡
ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ በተለይ አሁን እየፈፀመ ነው የሚለውን ሲያትትና ምክንያቱንም ሲያስረዳ ዜጎች ያለፈቃዳቸው የኢሕአዴግ አባል እንዲሆኑ እንደሚያስገድዳቸው የመኢአድ መግለጫ አመልክቷል፡፡
የሥራና የትምህርት ዕድል ማሣጣት፣ ማስፈራራትና ዛቻ መፈፀም፣ ከአገር ማሣደድ እና መሰወር፣ እንዲሁም ቅጥ ያጣ ስለላ ማካሄዱ ከመጭዎቹ ምርጫዎች አስቀድሞ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን አቅም በማሣጣት፣ ከተቻለም በማጥፋት ያለምንም ተቀናቃኝ አሸናፊ ለመሆንና ነፃ ምርጫ አካሄድኩ ለማለት አልሞ እየተንቀሣቀሰበት ያለ አካሄድ ነው ይላል፡፡
ስለሆነም ኢሕአዴግ የሰላማዊ ትግሉን ምሕዳር እያጠበበ መንቀሣቀስ ወደማይቻልበት ደረጃ አድርሶታል ሲል መግለጫው ገዥውን ፓርቲ ይከስሣል፡፡
የመኢአድ ዋና ፀሐፊ አቶ ተስፋዬ ታሪኩ ለቪኦኤ በሰጡት ቃለ ምልልስ ድርጅቱ የዛሬውን መግለጫ እንዲያወጣ የተገደደበትን ምክንያት ሲናገሩ ስንት የድርጅቱ አባላት የት የት እንደታሠሩ ዘርዝረዋል፡፡
የመለስካቸው አምኃን ዘገባ ያዳምጡ።