የሕንዱ ግዙፍ የታዳሽ ኃይል ማመንጫ አዳኒ በዩናይትድ ስቴትስ በጉቦ ቅሌት ተወነጀለ

ፎቶ ፋይል ፦ ሰራተኞች የፀሐይ ፓነሎችን እየጫኑ፣ በካቭዳ፣ ሕንድ፣

የሕንዱ ጠቅላይ ሚንስትር ናሬንድራ ሞዲ የታዳሽ የኃይል ምንጭ ግንባታ እቅድ ዋና ደጋፊ የሆኑት ቢሊየነሩ ጓታም አዳኒ፤ በዓለም ግዙፉ ይሆናል ለተባለው የታዳሽ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክታቸው የፈረንሳዩን ቶታል ኢነርጂ እና የካታር ኢንቨስትመንት ባለስልጣንን አጋርነት አግኝተዋል።

በተለየ ዓይን የሚያዩት የኩባንያቸው ዋነኛው ውጥን ‘አዳኒ ግሪን’ የተባለው በሕንዷ የምዕራብ ጉጅራት ግዛት የሚገኘው ፕሮጀክት እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር በ2030 ሲጠናቀቅ 50 ጊጋ ዋት ኃይል ማለትም ሕንድ በእቅድ ከያዘችው አጠቃላይ የንፁህ ኃይል ምርት ‘አንድ አስረኛውን ያህል ያመነጫል’ ተብሎ ይጠበቃል።

ይሁን እንጂ ያ እቅድ አሁን፤ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ አዳኒ እራሳቸው፣ የወንድማቸው ልጅ እና የኩባንያቸው ዋና ድሬክተር ሳጋር አዳኒ፤ እንዲሁም መራሄ ድሬክተሩ ቭኔት ኤስ ጃይን፤ ለህንድ ኃይል የሚያቀርብ የተቋራጭ ሥራ ኮንትራት ለማግኘት የ265 ሚሊዮን ዶላር ጉቦ በመስጠት እና የአሜሪካ ባለ ኃብቶችን በማሳሳት ወንጀሎች በቀረቡባቸው ክሶች መሰናክል ገጥሞታል።

የክሱ ዜና እንደተሰማም፣ የአዳኒ ግሪን የዎል ስትሪት ገበያ የአክሲዮን (ስቶክ) ዋጋ 36 በመቶ በማሽቆልቆሉ፣ ከገበያ ዋጋው 9ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር አጥቷል።

ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የቀረበበትን ክስ ‘መሠረተ ቢስ’ ሲል ውድቅ ያደረገው ‘አዳኒ ግሩፕ’ በበኩሉ ይህንን ለመቀልበስ ‘ሁሉንም የሕግ አማራጮች እጠቀማለሁ’ ብሏል ።

ይሁን እንጂ ሁኔታው ለታዳሽ ኃይል ግንባታ ፕሮጀክቱ ማቀላጠፊያ የሚያስፈልገውን ተጨማሪ ገንዘብ የማሰባሰብ ጥረቱን ያወሳስበዋል ተብሎ ተገምቷል።