በአይቮሪ ኮስት ትልቋ ከተማ አቢጃን በደረሰ የጎርፍና የመሬት መንሸራተት አደጋ ባለፉት 10 ቀናት ውስጥ ቢያንስ 24 ሰዎች መሞታቸው ተነግሯል።
በአራት እጥፍ የከበደ ዝናብ የምዕራብ አፍሪካዊቱን ሃገር የኢኮኖሚ መዲና ሲመታ፣ ከፍተኛ ጎርፍና የመሬት መንሸራተት ተከስቷል።
ከወዲያኛው ሳምንት ሐሙስ እስካለፈው ቅዳሜ በጣለው ዝናብ ቢያንስ 24 ሰዎች እንደሞቱ የሲቪሎችን ደህንነት የሚከታተለው መንግስታዊ ቢሮ አስታውቋል።
በጎርፍ የተወሰዱ ሁለት ተጨማሪ ሰዎች የደረሱበት አለመታወቁንም ቢሮው ጨምሮ ገልጿል።
ስድስት ሚሊዮን ነዋሪዎች ባሏት አቢጃን፣ አደገኛ ዝናብና ተከትሎ የሚመጣው ጎርፍ በተደጋጋሚ ይከሰታል። ድሆች ጎርፍ በሚያጠቃቸው አካባቢዎች እንደነገሩ በተሰሩ መጠለያዎች ውስጥ መኖራቸው ለአደጋው ተጋላጭ አድርጓቸዋል።
ባለፈው ዓመት በደረሰ ተመሳሳይ አደጋ 30 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።