ምዕራባዊያኑ ታንኮች እንዲልኩላት ዩክሬን ተማፀነች

  • ቪኦኤ ዜና
ቬልሲክ፣ ጀርመን

ቬልሲክ፣ ጀርመን

“ወታደሮቼ በሠራዊትም በመሣሪያም ይበልጥ ከታጠቀው የሩሲያ ኃይል ጋር ለመዋጋት እንዲችሉ ታንኮች ላኩልን” ስትል ዩክሬን ምዕራባውያን አጋሮቿን ተማፀነች።

የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲሚትሮ ኩሌባና የመከላከያ ሚኒስትሩ ኦሌክሲ ሬዝኒኮቭ ባወጡት የጋራ መግለጫ የሃገራቸውን የመከላከያ ኃይሎች ለማጠናከር ዕርዳታ የሰጡትን ሃምሣ ሀገሮች አመስግነዋል።

ቻሌንጀር 2 የሚባሉ ታንኮችን እንደምትልክ ለተነገረው ብሪታኒያ ሚኒስትሮቹ ምሥጋና አቅርበው የጀርመን ሌፐርድ (አነር) የሚባሉ ታንኮች ያሏቸው ሃገሮችም እንዲልኩላቸው ጠይቀዋል።

ዋሺንግተን አብራምስ የሚባሉ ታንኮቿን ለመላክ ከተስማማች በርሊንም ሌፐርድ 2 ታንኮችን እንደምትልክ የዩናይትድ ስቴትስና የጀርመን ባለሥልጣናት ገልፀዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ የመከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦስተን ጀርመን ሄደው ከአቻቸው ቦሪስ ፒስቶሪየስ ጋር እንደሚነጋገሩና ነገ፤ ዐርብ ደግሞ በዩናይትድ ስቴትስ የሚመራውን የዩክሬን መከላከያ ድጋፍ ትብብር ቡድን ስብሰባ እንደሚከፍቱ ታውቋል።

ዩናይትድ ስቴትስ ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎችን ጨምሮ ከ 2 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚገመት አዲስ የጦር መሳሪያ ድጋፍ እንደምትልክ ይፋ ታደርጋለች ተብሎ እየተጠበቀ ቢሆንም አብራምስ ታንኮችን እንደማያካትት ተሰምቷል።

ይህ በዚህ እንዳለ የአውሮፓ ፓርላማ ፕሬዚደንት ሻርል ሚሼል ከዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪና ከሌሎችም ባለሥልጣናት ጋር ለመወያየት ዛሬ ወደ ኪዪቭ እንደሚሄዱ አስታውቀዋል።