በአፍሪካ ቀንድ የምግብ እጥረት እና ሞት ያጠላባቸው ከ1.9 ሚ. በላይ ሕፃናት መኖራቸውን ዩኒሴፍ አስጠነቀቀ

Your browser doesn’t support HTML5

በአፍሪካ ቀንድ የምግብ እጥረት እና ሞት ያጠላባቸው ከ1.9 ሚ. በላይ ሕፃናት መኖራቸውን ዩኒሴፍ አስጠነቀቀ

በአፍሪካ ቀንድ፣ እስከ ዛሬ ታይቶ በማይታወቅ መጠነ ሰፊ ረኀብ፣ መፈናቀል፣ የውኃ ዕጦት እና ድህነት ውስጥ የሚገኙ፣ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የኾኑ ከሰባት ሚሊዮን በላይ ሕፃናት መኖራቸውን፣ ዓለም አቀፉ የሕፃናት መርጃ ድርጅት(ዩኒሴፍ)፣ ከትላንት በስቲያ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። ከእነርሱም ውስጥ፣ ከ1ነጥብ9 ሚሊዮን በላይ ሕፃናት፣ ለከፋ የምግብ እጥረት እና ለሞት ሊዳረጉ እንደሚችሉ፣ ዩኒሴፍ አስጠንቅቋል፡፡

ዩኒሴፍ በመግለጫው፣ ክልሉ ለሦስት ተከታታይ ዓመታት ካስተናገደው አስከፊ ድርቅ እያገገመ ቢኾንም፣ በአካባቢው ለሚገኙ ማኅበረሰቦች የእንስሳት፣ የሰብል እና የኑሮ ውድመት ምክንያት ኾኖ ማለፉን አመልክቷል፡፡

የዩኒሴፍ የምሥራቅ እና የደቡብ አፍሪካ አካባቢ ዲሬክተር መሐመድ ፎል፣ በምሥራቅ አፍሪካ ያለው ቀውስ፣ “ለሕፃናት ከፍተኛ ጉዳት አስከትሏል፤” ብለዋል፡፡

ዲሬክተሩ አክለውም፣ ባለፉት ሦስት ዓመታት፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕፃናት እና ቤተሰቦች፣ በሕይወት ለመቆየት ሲሉ፣ ለአደጋ ተጋላጭ በሚያደርጋቸው ኹኔታ፣ ምግብ እና ውኃ ፍለጋ መኖሪያ ቤታቸውን ለቀው ለመውጣት መገደዳቸውን ተናግረዋል፡፡

ይህም፣ እንደ ምግብ፣ መጠለያ፣ ውኃ እና ትምህርት ያሉ መሠረታዊ አስፈላጊ ነገሮችን እያሳጣቸው እንደኾነ፣ ዲሬክተሩ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

እንደ ዩኒሴፍ መግለጫ፣ አሁን የሚታየው ዝናም መጠነኛ እፎይታን ቢያመጣም፣ ደረቃማው መሬት ውኃውን አቁሮ ማስቀረት ባለመቻሉ፣ የጎርፍ አደጋ አስከትሏል። ይህም ለተጨማሪ መፈናቀል፣ ለበሽታ ተጋላጭነት፣ ለከብቶች እና ለሰብል ብክነት ምክንያት እንደኾነ አስረድቷል፡፡

በሶማልያ የጎርፍ መጥለቅለቅ፥ ቤቶችን፣ የእርሻ መሬቶችንና መሠረተ ልማቶችን ሲያወድም፣ ወደ 219ሺሕ የሚደርሱ ሰዎችን፣ ከቀዬአቸው አፈናቅሏል፤ 22 ሰዎችን ለሞት ዳርጓል። ኢትዮጵያም በጎርፍ ሳቢያ፣ ከፍተኛ ውድመት እና መፈናቀል አስተናግዳለች።

የጎርፍ አደጋው፣ ቀድሞውንም በድርቅ የተጎዱ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጋላጭነት አጠናክሯል፤ ተደራራቢ ተጽእኖም ፈጥሯል።

የኮሌራ በሽታ በብዙ ክልሎች ተዛምቶ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ከተመዘገቡት ረጅሙ ወረርሽኞች አንዱ ለመኾን መብቃቱ፣ በመግለጫው ተመልክቷል፡፡

በመላው ኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ሶማልያ፣ 23 ሚሊዮን ሰዎች ለከፋ የምግብ ዋስትና ዕጦት መዳረጋቸውም ተገልጿል።

አስከፊ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ያለባቸውና ሕክምና የሚሹ ሕፃናት ቁጥር፣ ካለፈው ዓመት በእጅጉ ከፍ ያለ ሲኾን፣ ይህም ዘላቂ ጉዳት እንዳለው ዩኒሴፍ በመግለጫው ጠቁሟል፡፡ “ሴቶች እና ሕፃናት፣ ለጾታዊ እና አካላዊ ጥቃት እንዲሁም ለጉልበት ብዝበዛ የመጋለጥ ዕድላቸው እየጨመረ ነው፤” ያለው መግለጫው፣ ቀጣይነት ያለው የኮሌራ፣ የኩፍኝ፣ የወባ እና የሌሎች በሽታዎች ወረርሽኝ፣ በአስከፊ የአየር ኹኔታ እና ደካማ የጤና ሥርዓቶች መባባሱን አስታውሷል፡፡

ዋጋው የናረ የምግብ ዋጋ፣ በአካባቢያዊ ገበያዎች ላይ ጫና ከማሳደሩም በላይ፣ ሕፃናትንና ቤተሰቦቻቸውን ለከፋ ጉዳት ያጋልጣል። የአየር ንብረት ቀውሱ፥ የጅምላ መፈናቀልን፣ የተመጣጠነ ምግብ እጥረትንና የበሽታዎችን አስከፊነት ያባብሳል፤ ብሏል፡፡

እ.ኤ.አ በ2022፣ የለጋሾች ድጋፍ፥ ከ30 ሚሊዮን በላይ ለሚኾኑ ሕፃናት እና እናቶች፣ የተመጣጠነ ምግብ እጥረትን ለመከላከል ማገዙን ያመለከተው ዩኒሴፍ፣ በዚኽ ዓመት፣ ተለዋዋጭ የገንዘብ ድጋፍ፣ ለሕፃናት ማገገሚያ ብቻ ሳይኾን፣ ቀጣይ የአየር ንብረት ተጽእኖዎችንና ድንገተኛ አደጋዎችን ለመቋቋም፣ ተከላካይ እና ዘላቂ ሥርዐቶችን ለማዘጋጀት ያለው አስፈላጊነትም በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡

በአፍሪካ ቀንድ ያለው አስከፊ የአየር ሁኔታ ለውጦችን በሚመለከት አፋጣኝ እርምጃዎች መወሰድ አለባቸው ሲል ይህ ተግባራዊ የማይሆን ከሆነ ግን ህጻናት እና ቤተሰቦች ሙሉ በሙሉ የማገገም እድል ከማግኘታቸው በፊት ቀጣዩ ቀውስ ሊመጣ ይችላል ሲል ማስጠንቀቁን መግለጫውን የጠቀሰው የአሶሴይትድ ፕሬስ ዘገባ አመልክቷል፡፡