በሱዳን የተኩስ አቁም ስምምነቱ ሳይከበር ቀረ

የሱዳን ጦር እና ፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ሰጪ ኃይሎች ለአንድ ሳምንት የሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምነት ካደረጉ በኋላም ዛሬ ግንቦት 15 ቀን 2015 ዓ.ም ካርቱም በጭስ ታፍናለች።

በአሜሪካና በሳዑዲ አረቢያ አደራዳሪነት የተደረሰውና፣ ትናንት ሰኞ ከምሽቱ ለአራት ሩብ ጉዳይ ይጀምራል የተባለው የሰባት ቀናት የተኩስ ማቆም ስምምነት፣ እንደ ከዚህ በፊቶቹ ስምምነቶች ኹሉ ተጥሶ፣ የሱዳን መዲና ካርቱም ዛሬ ማክሰኞም በፍንዳታ ስትናጥ ውላለች።

በሱዳን የተኩስ ማቆሙ በጀመረ በደቂቃዎች ውስጥ የአየር ድብደባ እና የተኩስ ልውውጥ እንደነበር የዓይን እማኞች ተናግረዋል። በሰሜን ካርቱም ውጊያ ሲካሄድ፣ ከካርቱም በሥተ ምስራቅ ደግሞ የአየር ድብደባ እንደነበር ታውቋል።

የከባድ መሣሪያ ተኩስ እየሰሙ እንደሆነ እና በደቂቃዎች ልዩነትም ፍንዳታ እንደሚሰማ አንድ የካርቱም ነዋሪ ለዜና ወኪሉ ተናግሯል።

በአንዳንድ የካርቱም ክፍሎች ደግሞ፣ የሚያስጨንቅ ጸጥታ ሰፍኖ እንደነበር እና ነዋሪዎቹም የሰላም ስምምነቱ ውጊያውን ያስቆማል በሚል ተስፋ አድርገው ነበር። ሕይወት አድን ርዳታ እንዲደርስ እና ወደ ጦር አውድማነት ከተቀየረችው ካርቱም በሕይወት ለመውጣት እንደሚሹም ታውቋል።

በጦር ሠራዊቱ ዋና አዛዥ ጀኔራል አብደል ፋታህ አል ቡርሃን እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ አዛዥ ሞሃመድ አምዳን ዳጋሎ መካከል ለአምስተኛ ሳምንት በቀጠለው ውጊያ፣ እስከ አሁን 1ሺህ የሚሆኑ ሰዎች እንደሞቱ ሲገለጽ፣ ከሚሊዮን በላይ የሚኾኑት ደግሞ ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል። 250 ሺሕ የሚሆኑትን ደግሞ ወደ ጎረቤት አገራት እንዲሸሹ አድርጓል።

ነዋሪዎች ውሃ፣ ምግብና መሠረታዊ ፍጆታዎች እያለቁባቸው ነው ተብሏል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚለው ደግሞ፣ ጦርነቱ ከሱዳን ሕዝብ ግማሽ የሚሆነውን 25 ሚሊዮን ሕዝብ የሰብዓዊ ርዳታ ጠባቂ አድርጓል።