በሱዳን ከሶስት ቀናት ተኩስ ማቆም በኋላ ውጊያው ቀጥሏል

ታዳጊው ከዳቦ ሱቅ ገዝቶ ወደ ቤቱ እያመራ ካርቱም፣ ሱዳን እአአ 6/21/2023

ታዳጊው ከዳቦ ሱቅ ገዝቶ ወደ ቤቱ እያመራ ካርቱም፣ ሱዳን እአአ 6/21/2023

የ72 ሰዓታት የተኩስ ማቆም በተጠናቀቀ በደቂቃዎች ውስጥ፣ የሱዳን መዲና ካርቱም ዛሬ ማለዳ በከባድ መሣሪያ ተኩስ ተንጣለች፡፡

ከተኩስ ማቆሙ ፍጻሜ ቀደም ብሎ ማክሰኞ ምሽት፣ የሱዳን የስለላ ተቋም በእሳት ጋይቷል። ለእሳት ቃጠሎው አንዱ ተፋላሚ ወገን ሌላውን ይከሳል።

በአብደል ፋታህ አል ቡርሃን በሚመራው የሱዳን ሠራዊት ውስጥ ያሉ አንድ ምንጭ፣ ለእሳቱ የሞሃመድ ሃምዳን ደጋሎን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ተጠያቂ አድርገዋል። በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ውስጥ ያሉ ሌላ ምንጭ ደግሞ ፣ የኃይሉ ወታደሮች ተሰባስበው በሚገኙበት የስለላ ተቋም ላይ ሠራዊቱ በድሮን ጥቃት ፈጽሟል ሲሉ ለኤኤፍፒ ዜና ወኪል ተናግረዋል።

ከናይል ባሻገር ባለችው ኦምዱርማን ከተማ ያሉ ነዋሪዎች ደግሞ ዛሬ ማለዳ የከባድ መሣሪያ ልውውጥ መስማታቸውን ተናግረዋል። የጦር አውሮፕላኖችም ዝቅ ብለው ሲበሩ ነበር ብለዋል።በአሜሪካ እና በሳዑዲ አረቢያ አማካኝነት የተደረሰው የ72 ሰዓታት ተኩስ ማቆም፣ በውጊያው ምክንያት መንቀሳቀስ ላልቻሉት ሱዳናውያን መጠነኛ እፎይታ ሰጥቶ ነበር ተብሏል።

ሌላው የጦር አውድማ ከሆነችው ዳርፉር ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ነዋሪዎች ግጭቱን በመሸሽ ለቀው እየወጡ መሆኑም ታውቋል።