ሶማሌያ ያደረገችውን ኢኮኖሚያዊ እና ተቋማዊ ማሻሻያዎችን ተከትሎ፣ የዕዳ አከፋፈል እፎይታ ማግኘት እንደምትችል፣ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) እና የዓለም ባንክ ቢያስታውቁም፣ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት(IMF) እና ከሌሎችም የባለብዙ ወገን አበዳሪዎች፣ ሙሉ ብድር የማግኘት ተስፋዋን አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል ስጋት እንዳለባት ባለሞያዎች አስጠንቅቀዋል፡፡
የአሜሪካ ድምፅ ያነጋገራቸው የኢኮኖሚ እና የፋይናንስ ባለሞያዎች፣ በሶማልያ የፌዴራል መንግሥት እና በፑንትላንድ የፌዴራሉ አባል ግዛቶች መካከል፣ በዐዲስ መልክ የተፈጠረ የፖለቲካ አለመግባባት፣ የገቢ አሰባሰብ እና የፊስካል ግልጽነትን ማሳደግ ካለመቻሉ ጋራ ተያይዞ፣ ሶማሊያ፣ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት(IMF) እና ከሌሎች የባለብዙ ወገን አበዳሪዎች፣ ሙሉ ብድር የማግኘት ተስፋዋን አደጋ ላይ ሊጥለው እንደሚችል ስጋታቸውን ይገልጻሉ፡፡
የግዥ ሥርዐቱ በግልጽ ውድድር ላይ የተመሠረተ አለመኾኑ፣ በማዕከላዊው መንግሥት መዋቅሮች እና በፌዴራሉ አባል ግዛቶች መካከል፣ በፊስካል ፌደራሊዝም ላይና በበርካታ የነዳጅ እና ጋዝ ስምምነቶች ግልጽነት አለመኖር፣ ሶማልያ የገጠሟት ተጨማሪ ፈተናዎች መኾናቸውን ባለሞያዎቹ አስታውቀዋል፡፡
የዕዳ ክፍያ እፎይታን ብቻ ሳይኾን፣ ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት ተጨማሪ ብድር እንድታገኝ ከተፈለገ፣ የፊስካል ግልጽነትን ማጠናከር ይጠበቅባታል፤”
የቀድሞው የሶማልያ ፕሬዚዳንት አማካሪ የነበሩት ሑሴን አቡዲካሪም፣ ሶማልያ “የዕዳ ክፍያ እፎይታን ብቻ ሳይኾን፣ ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት ተጨማሪ ብድር እንድታገኝ ከተፈለገ፣ የፊስካል ግልጽነትን ማጠናከር ይጠበቅባታል፤” ብለዋል፡፡
ሶማልያ፣ ከውጭ አበዳሪዎች ያለባት ዕዳ፣ ከአምስት ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሚኾን ሲገመት፣ ከዚኽ ውስጥ ትልቋ አበዳሪ የኾነችው ዩናይትድ ስቴትስ፣ አንድ ቢሊዮን ዶላር እንደሚደርስ ተነግሯል፡፡
ሶማልያ፣ እአአ የካቲት 2020 ያደረገችውን የኢኮኖሚ እና ተቋማዊ ማሻሻያዎችን ተከትሎ፣ በዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም እና በዓለም ባንክ ተነሣሽነት፣ የብድር አከፋፈል እፎይታ እንዲያገኙ ከተፈቀደላቸው ከፍተኛ ባለዕዳ ከኾኑ ድኻ ሀገራት(HIPC) የብድር እፎይታ ለማግኘት ብቁ ኾናለች። በሶማልያ ትልቅ ፈተና ከኾኑት መካከል፣ ሙስና አንዱ መኾኑም ተጠቅሷል፡፡
ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ መሐሙድ፣ የሶማልያን የፋይናንስ ተቋማት ሕጋዊነት እና ተኣማኒነት ለማሳደግ ያለመ፣ የፀረ ሙስና መመሪያዎችን ተፈራርመዋል።
መመሪያዎቹ፥ ሙስናን መዋጋት፣ ተጠያቂነትን ማጎልበት፣ የመንግሥት የፋይናንስ አስተዳደር ሥርዓቶችን ማጠናከር፣ የመንግሥትን ተቋማት ቅልጥፍናና ውጤታማነት ማሻሻል ይገኙበታል።
የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ቦርድ፣በመጪው ታኅሣሥ ወር፣ ከሶማልያ ጋራ ያለውን የሠራተኛ ደረጃ ስምምነት ይገመግማል ተብሎ ይጠበቃል።