ሩስያ በጠፈር ላይ ባካሄደችው የጦር መሳሪያ ሙከራ ወደ 1ሺ500 የሚደርሱ ስብርባሪ ቅሪቶችን በመተው በጠፈር ምርምር ላይ የሚገኙ ዓለም አቀፍ የጠፈር ተመራማሪ ሳይንቲስቶችን ለአደጋ አጋልጣለች ተብሎ የቀረባበትን ክስ የሩስያ ባለሥልጣናት ዛሬ ባወጡት መግለጫ አስተባብለዋል፡፡
የዩናይትድ ስቴትስ ባለሥልጣናት ትናንት ሰኞ ባወጡት መግለጫ ሩሲያ አሮጌ ሳተላይቷን በሚሳየሏ ለማውደም ያደረገችው ሙከራ እጅግ አደገኛና ኃላፊነት የጎደለው እምርጃ ነው ሲሉ ከሰዋል፡፡
በጠፈር ላይ የተበተኑት ፍርስራሾች፣ በምድር ዙሪያ፣ በሰዓት 28ሺ ኬሎ ሜትር በመብረር ላይ ለሚገኙት የጠፈር ምርምር ጣቢያዎች እጅግ አደገኛ መሆናቸው ተመልክቷል ሲል አሶሼይትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር በዛሬው መግለጫው፣ ሙከራውን ማድረጉንና ሳይተላይቱንም ማወደሙን አስታውቆ፣ ይሁን እንጂ “ዩናይትድ ስቴትስ የቀሩት ስብርባሪ ቅሪቶች ተሽከርካሪዎቹን የጠፈር ጣቢያዎችና የጠፈር መንኮራኩሮችን ወይም የጠፈር ምርምሮችን ያልጎዱና የማይጎዱ መሆኑን ታውቃለች” ብሏል፡፡ የዩናይትድ ስቴትስ ባለሥልጣናትን መግለጫ “ግብዝነት” ብሎታል፡፡