በጀርመን የተጨፈጨፉ ናሚቢያውያን መታሰቢያ ሊደረግላቸው ነው

በጀርመን ቅኝ ገዢ ሃይሎች የተጨፈጨፉትን በአስር ሺሕ የሚቆጠሩ ናሚቢያውያንን ለማሰብ የሰለባዎቹ ተወላጆች ሉደሬትዝ በተባለችው ከተማ በዚህ ሣምንት መጨረሻ እንደሚሰባሰቡና የመታሰብያ ሃውልትም እንደሚመርቁ ታውቋል።

በናሚቢያ ሻርክ ደሴት ተብሎ በሚጠራው ሥፍራ ቅኝ ግዛትን የተቃወሙ በሺህ የሚቆጠሩ ናሚቢያውያንን የጀርመን ቅኝ ግዛት ኃይሎች በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ ሰብስበው ጨፍጭፈዋቸው ነበር። ሕጻናትም ከሰለባዎቹ መሃል ናቸው።

አንዳንድ የታሪክ ባለሙያዎች፣ “የሃያኛው ክፍለ ዘመን የመጀመሪያው የዘር ማጥፋት” ብለው ለሚጠሩት ጭፍጨፋ የናሚቢያ መንግሥት የመታሰቢያ ቀን አላወጀም።

አካባቢው አሁን በመንግሥት የሚተዳደር የመዝናኛ ስፍራ ሆኖ እያገለገለ ሲሆን፣ የሰለባዎቹ ተወላጆች ሥፍራው የመዝናኛ ቦታ መሆኑ አስቆጥቷቸዋል።

በእአአ 1904 የጀርመን ወታደሮች 80 ሺህ የሚሆኑ ሄሬሮ በመባል የሚጠሩ የአገሬው ጎሳ አባላትን በካላሃሪ በረሃ ላይ አሳደው ሴቶቹን ሲደፍሩ፣ የማረኳቸውን ደግሞ አርደዋል። በዓመቱ ደግሞ ናማ የተባሉት ጎሳዎች እንዲጠፉ የጀርመኑ ሠራዊ አዛዥ ተዕዛዝ አስተላልፎ ነበር።

60 ሺሕ ሄሬሮዎችና 10 ሺሕ የሚሆኑ ናማዎች መጨፍጨፋቸውን የኤኤፍፒ ዘገባ አመልክቷል።