በዓለም ዙሪያ የሚታወቀው አሜሪካዊው የፈጣን ምግብ ድርጅት ማክዶናልድስ በሩሲያ ወራራ ምክንያት ካለፈው መጋቢት ጀምሮ ዩክሬን ውስጥ አቋርጦት የነበረውን አገልግሎት መልሶ ለመጀመር ማቀዱን አስታውቋል።
ድርጅቱ ውሳኔው ላይ የደረሰው ከዩክሬን ባለሥልጣናት፣ ከአቅራቢ ድርጅቶችና ከደኅንነት ባለሙያዎች ጋር ሰፊ ምክክር ካደረገ በኋላ መሆኑን የድርጅቱ የዓለም አቀፍ አገልግሎት ዘርፍ ከፍተኛ ምክትል ፕሬዚዳንት ፖል ፓምሮይ ለሠራተኞቻቸው ትናንት ሃሙስ በበተኑት መግለጫ አስታውቀዋል።
ማክዶናልድስ ወደ ሥራቸው ለመመለስ “ከፍተኛ ፍላጎት” ያላቸውን ከአሥር ሺህ በላይ ዩክሬናዊያን የድርጅቱ ሠራተኞችን ፍላጎትም ግምት ውስጥ ማስገባቱን ፓምሮይ ጨምረው ገልፀዋል።
ማክዶናልድስ ለድርድጅቱ ሠራተኞች እስከ አሁን ደመወዝ እየከፈለ መሆኑን መግለጫው አመልክቷል።
ሌሎች ዓለም አቀፍ የንግድ ድርጅቶች ወደ ዩክሬን ተመልሰው ከጦርነቱ ርቀው በሚገኙ አካባቢዎች ለመሥራት ማሰባቸውንም የአሶሲየትድ ፕሬስ ዘጋቢዎች አመልክተዋል።
የዩክሬን ኢኮኖሚ በዚህ ዓመት በ33 ከመቶ ሊቀነስ እንደሚችል ዓለምአቀፉ የገንዘብ ድርጅት አመልክቷል።