ሟቾቹ ኢትዮጵያውያን ሊሆኑ ይችላሉ የተባለ የጅምላ መቃብር በማላዊ ተገኘ

  • ቪኦኤ ዜና
 ሉሎንግዌ፣ ማላዊ

ሉሎንግዌ፣ ማላዊ

የማላዊ ፖሊስ ኢትዮጵያውያን ፍልሠተኞች ሊሆኑ ይችላሉ ያላቸውን የ25 ሠዎች አስከሬን በጅምላ ተቀብሮ ማግኘቱን ትናንት አስታውቋል።

“መቃብሩ የተገኘው ማክሰኞ ነበር። በማግሥቱ የአጥር ከለላ አበጅተን አስከሬኖቹን ቆፍርን ማውጣት ጀመርን። እስከአሁን 25 አስከሬኖችን አውጥተናል” ሲሉ የፖሊስ ቃል አቀባዩ ፒተር ካላያ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

ፖሊስ ወሬውን ያገኘው ከሉሎንግዌ በስተሰሜን 250 ኪሜ እርቀት ላይ ከምትገኝ "ምዚምባ" በተባለች መንደር ካሉ ነዋሪዎች እንደሆነ ታውቋል። ነዋሪዎቹ የዱር ማር ቆረጣ ላይ ሳሉ ድንገት ሰዎቹ የተቀበሩበት ሥፍራ ማግኘታቸው ታውቋል።

“በማላዊ በኩል ወደ ደቡብ አፍሪካ ሊሻገሩ የሞከሩ ሕገ-ወጥ ሠደተኞች እንደሆኑ እንጠረጥራለን” ብለዋል ፒተር።

ከሥፍራው በተገኘው መረጃ መሠረትም ሟቾቹ እድሜያቸው ከ25 እስከ 40 የሆኑ ኢትዮጵያውያን ናችው ብለዋል ፒተር።

እየፈረሰ ያለው በድን ተቆፍሮ ከወጣ በኋላ ለምርመራ መላኩም ታውቋል።

በግምት ካለፈው አንድ ወር ወዲህ የተቀበሩ ይመስላል ብለዋል የፖሊሱ ቃል አቀባይ ፒተር።

ከአህጉሪቱ በተሻለ በኢንዱስትሪ የበለጸገችው ደቡብ አፍሪካ ከምሥራቅ አፍሪካና ከሌሎች የአህጉሪቱ ክፍሎች ለሚነሱ ድህነት ለተጫናቸው ስደተኞች መስህብ ነች። ማላዊ ደግሞ ተመራጭ አቋራጭ ነች።

ፒተር ካላያ እንዳሉት በዚህ ዓመት ከጥር እስከ መስከረም ባለው ግዜ ውስጥ ብቻ 221 ሕገ-ወጥ ፍልሰተኞችን ማላዊ ድንበሯን አቋርጠው ሲያልፉ ይዛለች። ከእነዚህ ውስጥ 186ቱ ኢትዮጵያን ናቸው።