በኢትዮ-ጅቡቲ መሥመር የሚመላለሱ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች፣ በታጣቂዎች ይደርስብናል ያሉት ጥቃት እየተባባሰ መምጣቱን ለአሜሪካ ድምፅ አስታወቁ፡፡
አሽከርካሪዎችን አፍኖ በክፍያ ከመደራደር ጀምሮ፣ ተኩስ ከፍቶ እስከ መግደል እና የአካል ጉዳት እስከ ማድረስ የሚዘልቅ ተደጋጋሚ ችግር እየተስተዋለ መኾኑን፣ አሽከርካሪዎቹ ገልጸዋል፡፡
የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር፣ ለደኅንነት ስጋታቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ እልባት እንደሚሰጥ ቃል ቢገባም፣ ከዕለት ወደ ዕለት የሚፈጸምባቸው ጥቃት ተባብሶ መቀጠሉን አሽከርካሪዎቹ ያመለክታሉ፡፡
በአገሪቱ ልዩ ልዩ አካባቢዎች የሚስተዋለውን የጸጥታ መደፍረስ ተከትሎ፣ በአሽከርካሪዎች ላይም ጥቃቶች መበራከታቸውን ያረጋገጠው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፣ ጉዳዩ እንደሚያሳስበው ገልጿል፡፡
የአሜሪካ ድምፅ ያነጋገራቸው የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች፣ ባለፉት አንድ ወር ከዐሥራ አምስት ቀናት ውስጥ፣ እነርሱ የሚያውቋቸው አምስት አሽከርካሪዎች እና ረዳቶቻቸው፣ ማንነታቸው በአልታወቁ ታጣቂዎች ከታፈኑ በኋላ መገደላቸውን ተናግረዋል፡፡
በጅቡቲ መሥመር ለ20 ዓመታት በከባድ መኪና አሽከርካሪነት እንደሠሩ የሚናገሩት እና ለደኅንነቴ ሲባል ስሜም አይጠቀስ ድምፄም ይቀየር ያሉ አስተያየት ሰጪ፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ መሥመሩ፣ ለአሽከርካሪዎችም ኾነ ለተሳፋሪዎች የስጋት ምንጭ እንደኾነ ገልጸዋል፡፡
SEE ALSO: ድንበር ተሻጋሪ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ለጥቃት መጋለጣቸውን ገለፁአሽከርካሪዎችን አፍኖ በክፍያ ከመደራደር አንሥቶ፣ ተኩሶ እስከ መግደል እና የአካል ጉዳት እስከ ማድረስ የሚዘልቁ ተደጋጋሚ ችግሮች እየተስተዋሉ መኾኑን አሽከርካሪው አክለው ጠቁመዋል፡፡
ሌላው አስተያየት ሰጪም፣ ለ16 ዓመታት በድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪነት ከአገለገሉ በኋላ፣ በጸጥታው ችግር ምክንያት ሥራቸውን ለማቆም መገደዳቸውን ይናገራሉ፡፡
ከአሽከርካሪዎቹ ጋራ ተወያይቷል የተባለውን የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር አመራርም ኾነ የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ለማግኘት ጠይቀን፣ በቅርቡ በሚኒስቴር መ/ቤቱ፣ ለብዙኃን መገናኛ ዝርዝር መረጃ እንደሚሰጥ ከመጠቆም ባለፈ፣ ለጥያቄአችን ቀጥተኛ ምላሽ አላገኘንም፡፡
ሥራቸውን ለማቆም እንደተገደዱ የሚናገሩት አሽከርካሪ፣ ችግሩ ከመቀነስ ይልቅ እየጨመረ መምጣቱን ጠቁመዋል፡፡
በሥራ ላይ ያሉት አሽከርካሪ ደግሞ፣ የጸጥታውን ችግር ተከትሎ ስጋት ውስጥ የገቡ አሽከርካሪዎች፣ ለትራፊክ አደጋ እየተጋለጡ መኾናቸውን አመልክተዋል፡፡
SEE ALSO: አገር አቋራጭ አሽከርካሪዎች እየታገቱ እስከ 700 ሺህ ብር ይጠየቃሉችግሩ፣ በድንበር ተሻጋሪ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ሳይወሰን፣ በአገር ውስጥ የሕዝብ ማመላለሻ አሽከርካሪዎች እና ተሳፋሪዎች ላይም እየደረሰ እንደኾነ ያስረዳሉ፡፡
በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የሕግ እና ፖሊሲ ዲሬክተር ታሪኳ ጌታቸው፣ በአሽከርካሪዎቹ የቀረበው ቅሬታ፣ በልዩ ልዩ የአገሪቱ ክፍል የሚስተዋለው የጸጥታ መደፍረስ ያስከተለው ችግር እንደኾነ ይናገራሉ፡፡ ይህም ተቋማቸውን እንደሚያሳስበው ገልጸዋል፡፡
ከጸጥታ መደፍረስ ጋራ ተያይዞ የሚደርሰው ሰብአዊ ቀውስ መፍትሔ እንዲፈለግለት፣ ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ማሳሳባቸውንም ዲሬክተሯ ጠቁመዋል፡፡
ዲሬክተሯ፣ መንግሥት፥ ሰላም የማስፈን ሓላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ በወሎ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት መምህሩ ዶክተር አማረ ምትኩ፣ የአካባቢው ጸጥታ ካልተረጋገጠ፣ በተለይ የትራንስፖርት ዘርፉ በጸጥታዊ ችግሮች ሲታወክ፣ በወጪ እና ገቢ ንግዱ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ሊያስከትል እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡
የትራንስፖርት ዘርፉ ያለውን ዕሤት እና ዐቅም አስመልክቶ፣ ከሦስት ዓመት በፊት፣ በዐዲስ አበባ በተደረገ አገር አቀፍ ሴሚናር ላይ የቀረበ አንድ ጥናታዊ ጽሑፍ እንዳመለከተው፣ ከ95 በመቶ የሚልቀው የኢትዮጵያ የወጪ እና የገቢ ንግድ የሚሳለጠው በኢትዮ-ጂቡቲ መተላለፊያ(ኮሪደር) ነው፡፡