የ“ደቡብ” ክልል መዋቅርን ይፋዊ ፍጻሜ ያረጋገጠው የወላይታ ዞን ሕዝበ ውሳኔ ውጤት ተገለጸ

Your browser doesn’t support HTML5

የ“ደቡብ” ክልል መዋቅርን ይፋዊ ፍጻሜ ያረጋገጠው የወላይታ ዞን ሕዝበ ውሳኔ ውጤት ተገለጸ

በወላይታ ዞን በድጋሚ በተካሔደው፣ የጋራ ክልል ምሥረታ ሕዝበ ውሳኔ ላይ፣ ድምፅ ከሰጡ ነዋሪዎች መካከል፣ ከጥቂቶች በስተቀር አብዛኛዎቹ ወላይታን ጨምሮ፣ ስድስት ዞኖች እና አምስት ልዩ ወረዳዎች፣ በጋራ የሚመሠርቱትን ክልል እንደ ደገፉ፣ ምርጫ ቦርድ ይፋ አድርጓል።

የውሳኔ ሕዝቡ ውጤት፣ “የደቡብ ኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች” በሚል ስያሜ ይታወቅ የነበረው ፌዴራላዊ ክልል፣ በይፋ መፍረሱን ያረጋገጠ ነው፤ ሲሉ፣ የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁሩ አቶ ዳያሞ ዳሌ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የሽግግር መንግሥት ወቅት፣ ብሔራዊ ክልላዊ የሽግግር መስተዳድሮችን ለማቋቋም በወጣው ዐዋጅ ቁጥር 7/1984 መሠረት፣ ከክልል 7 እስከ 11 የነበሩ አምስት ክልሎች ከተቋቋሙ ከሁለት ዓመት በኋላ ወደ አንድ በመሰባሰብ ነበር፣ የደቡብ ክልል የተመሠረተው።

ከ1986 ዓ.ም ጀምሮ፣ በአምስት ክልሎች ስብስብ ተመሥርቶ፣ 56 ብሔር ብሔረሰቦችን በአንድነት አቅፎ ለ30 ዓመታት ያህል የቆየው፥ የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል፣ አሁን ወደተለያዩ ክልሎች ተዋቅሮ ህልውናውን ወደ ማጣት ተቃርቧል።

ከምሥረታው ጀምሮ እስከ አሁን፣ በአንድነት ከአቀፋቸው የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች፣ አንዴ ሞቅ ሌላ ጊዜ ቀዝቀዝ የሚሉ የአደረጃጀት ጥያቄዎችን ሲያስተናግድ ቆይቶ፣ ከሲዳማ ክልል ምሥረታ ጀምሮ መፍረሱን ተያያዘው።

ከሲዳማ ቀጥሎ፣ የተለያዩ ዞኖችንና ልዩ ወረዳዎችን ያቀፈው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል፣ የአገሪቱ 11ኛ ክልል ኾኖ ከአንድ ዓመት በፊት ሲመሠረት፣ አሁን ደግሞ፣ ኮንሶ፣ ወላይታ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ጋሞ፣ ጎፋ፣ ጌዴኦ ዞኖችን እንዲሁም፤ ቡርጂ፣ ባስኬቶ፣ አሌ፣ ደራሼ እና አማሮ ልዩ ወረዳዎችን አሰባስቦ፣ “የደቡብ ኢትዮጵያ” ክልል የሚል ስያሜ እንደሚኖረው የሚነገርለት ዐዲስ ክልል ለመመሥረት የሚያስችል፣ የሕዝበ ውሳኔ ውጤት ይፋ ኾኗል።

ምርጫ ቦርድ፣ የተለያዩ ግድፈቶችን አግኝቼበታለኹ፤ ብሎ፣ በድጋሚ ያደረገውን የወላይታ ዞን ሕዝበ ውሳኔ የመጨረሻ ውጤት፣ ትላንት፣ ሰኔ 20 ቀን 2015 ዓ.ም. ይፋ አድርጓል፡፡ በዚኽም፣ ከድምፅ ሰጪዎቹ እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው፣ የዐዲሱን ክልል ምሥረታ መደገፋቸውን ያመለክታል።

ይህ ውጤት፣ የነባሩን የ56 ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል መፍረስ በይፋ ያረጋገጠ ነው፤ ሲሉ፣ ለአሜሪካ ድምፅ የተናገሩት፣ የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁሩ አቶ ዳያሞ ዳሌ፣ ኾኖም፣ ዐዲስ የሚመሠረቱት ክልሎች ሕጋዊ ቅቡልነት ጉዳይ፣ አጠያያቂ ሊኾን እንደሚችል አመልክተዋል፡፡ በነባሩ ክልል ይነሡ የነበሩ የሕዝብ ጥያቄዎችን መመለስ ካልቻሉ፣ ፈተና እንደሚበዛባቸው፣ ምሁሩ ያስረዳሉ።

ባለሞያዎቹ በዚኽ ጉዳይ ላይ የሰጡትን አስተያየት፣ ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።