በኢትዮጵያ አንድ ተጨማሪ ክልል ተመሠረተ

የኢትዮጵያ ፌዴሬሽን ም/ቤት አባላት

የኢትዮጵያ ፌዴሬሽን ም/ቤት አባላት

የኢትዮጵያ ፌዴሬሽን ም/ቤት ትላንት ባካሄደው ስብሰባ “የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል” ተብሎ የተሰየመ ለአገሪቱ 12ኛ የሆነ አዲስ ክልል መመሥረቱን ይፋ አድርጓል።

በብሔረሰቦች ብዝሃነት የሚታወቀውና ‘የደቡብ ኢትዮጵያ ብሔር ብሄረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል’ ተብሎ ይጠራ በነበረው ክልል ውስጥ የነበሩ ዞኖች እና ሌሎችም አስተዳደሮች ባለፈው የካቲት ባደረጉት ሕዝበ ውሳኔ እና በቅርቡ የተካሄደው የወላይታ ዞን ዳግም ውሳኔ ሕዝብ ይፋ ከተደረገ በኋላ አዲስ ክልል ተመሥርቷል።

አዲሱ ‘የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል’፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ከአምስት ዓመታት በፊት ወደ ሥልጣን ከወጡ ወዲህ የተመሠረተ ሦስተኛ ክልል ነው።

የፌዴሬሽን ም/ቤቱ የአዲሱን ክልል ምሥረታ በሙሉ ድምጽ ማጽደቁን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። “ስድስት ዞኖች እና ሌሎች አምስት ልዩ አስተዳደሮች ውስጥ የሚገኙ ሕዝቦች ፍላጎታቸውን ባደረጉት ሕዝበ ውሳኔ በገለጹት መሠረት በአንድ የክልል መንግሥት እንዲዋቀሩ ተወስኗል” ሲል ምክር ቤቱ ባወጣው መግለጫ።

‘ሲዳማ’ እና ‘ደቡብ ምዕራብ’ የተሰኙ ክልሎች ከሁለት ዓመታት በፊት መመሥረታቸው ይታወሳል።