በትግራይ ክልል የተጀመረው ዘመቻ ውሱን ግብ እንዳለው ኢትዮጵያ አስታወቀች

  • ቪኦኤ ዜና

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የጀመረው የጦር ዘመቻ «ግልጽ፣ የተወሰነ እና የሚሳካ ግብ» እንዳለው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስታወቁ።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የጹሑፍ መልዕክት የተነበበው፤ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ በትግራይ ክልል ውስጥ የተቀሰቀሰው ፍልሚያ በእጅጉ እንዳስደነገጣቸው ካስታወቁ በኋላ ነው።

ሁለት ቀናትን ከፈጀ የፌዴራል መንግሥቱ እና ሃገሪቱን ለዐስርት ዓመታት የመራው ጠንካራ በብሄር የተደራጀ ቡድን ግጭት በኋላ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ከመላው የሃገሪቱ ክፍሎች ጦር በማደራጀት ወደ ትግራይ ክልል እያዘመተ እንደሚገኝ ሮይተርስ በዘገባው ላይ አስፍሯል።

በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የሚደረገው ዘመቻ ‘ ግልጽ፣ የተወሰነ እና የሚሳካ ግብ» እንዳለው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስታወቁት ደግሞ በትዊተር ገጻቸው በኩል ነው።

የአሁኑ ዘመቻ ፣ የሕግ የበላይነትን እና ሕገ መንግስታዊ ሥርዓትን ለመመለስ፣ በየትኛውም የሃገሪቱ ክፍል ያሉ ኢትዮጵያዊያን ሰላማዊ ሕይወት እንዲመሩም ለማስቻል የወጠነ መሆኑንም አክለዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዥ ፤በጦርነቱ መቀስቀስ ክፉኛ መደንገጣቸውን አስታውቀዋል።

ዛሬ አርብ በትዊተር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት፤ “የኢትዮጵያ መረጋጋት ለመላው የአፍሪቃ ቀንድ ቀጠና ጠቃሚ ነው። ውጥረቶች እንዲረግቡ እና ሰላማዊ መፍትሄ እንዲገኝ ጥሪ አቀርባለሁ" ብለዋል።

አብዱራፊ በተባለችው በትግራይ እና አማራ ክልል ድንበሮች አቅራቢያ ሌሊት ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ የተኩስ ድምጽ ይሰማ እንደነበረ አንድ የሰብአዊ ድጋፍ ሠራተኛ እንደነገሩት ሮይተርስ አክሎ ዘግቧል።