የበረራ ቡድን ማገዱን የኢትዮጵያ አየር መንገድ አስታወቀ

  • ቪኦኤ ዜና

በበረራ ላይ እያሉ ለትራፊክ ቁጥጥር ምላሽ ያልሰጡ የበረራ ሠራተኞችን ከሥራ ማገዱን የኢትዮጵያ አየር መንገድ አስታወቀ።

ከኻርቱም ወደ አዲስ አበባ ሲበር የነበረ በበረራ ቁጥር ET343 የተመዘገበ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አይሮፕላን ሰኞ፤ ነኀሴ 9/2014 ዓ.ም አዲስ አበባ ከሚገኘው የአየር ትራፊክ መቆጣጠሪያ ጋር ያለው ግንኙነት ለአጭር ጊዜ ተቋርጦ እንደነበር የሚጠቁም ሪፖርት እንደደረሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በፌስቡክ ገፁ አመልክቷል።

አየር መንገዱ በመልዕክቱ ላይ ግንኙነቱ የተቋረጠበትን ምክንያትና የጊዜ ርዝመት ባይገልፅም አይሮፕላኑ ግን በሰላም ማረፉን አመልክቷል።

ይሁን እንጂ በንግድ የአየር ማጓጓዣ ዘርፍ የሚስተዋሉ አደጋዎችንና ሌሎች ክስተቶችን የሚዘግበው “አቪዬሽን ሄራልድ” የሚባል ዌብሳይት “አብራሪዎቹ በወቅቱ እንቅልፍ ጥሏቸው እንደነበረ” ተናግሯል።

አቪዬሺን ሄራልድ ትናንት ሐሙስ፤ ነኀሴ 12 በዌብ ገፁ ላይ ባወጣው ዘገባ “የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737-800 በET-AOB የተመዘገበ የበረራ ቁጥር ET-343 ከኻርቱም (ሱዳን) ወደ አዲስ አበባ (ኢትዮጵያ) በFL370 በበረራ ላይ እያለ አብራሪዎቹ እንቅልፍ ወስዷቸው ነበር” ብሏል።

የአየር ትራፊክ ቁጥጥር ክፍሉ ከአብራሪዎቹ ጋር ለመገናኘት በተደጋጋሚ ያደረገው ሙከራ እንዳልተሳካለት ያስነበበው አቪዬሽን ሄራልድ ዘግየት ብሎም የአውቶፓይለቱ ወይም አይሮፕላኑን በራሱ እንዲበርር የሚያደርገው ቴክኖሎጂ ግንኙነት መቋረጡን ጠቅሷል። ያ ግንኙነት ሲቋረጥ መሣሪያው የሚያወጣው ድምፅ አብራሪዎቹን እንደቀሰቀሳቸውና አይሮፕላኑን ያለ ክፉ አጋጣሚ እንዳሣረፉትም አብራርቷል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግን በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ምርመራ እንደሚደረግና ምርመራው እስከሚጠናቀቅም “የበረራ ሠራተኞቹ ታግደው እንደሚቆዩ” ከመጠቆም በስተቀር ግንኙነቱ ስለተቋረጠበት ምክንያት በራሱ በኩል ያለውን መረጃ እስከአሁን አላሳወቀም።

“ደኅንነትን ማስጠበቅ የሁልጊዜም የመጀመሪያ ተግባሬ ነው” ያለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በምርመራው ውጤት መሠረት የእርምት እርምጃ እንደሚወሰድም አስታውቋል።

የአሜሪካ ድምፅ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት እየጣረ ነው።

Your browser doesn’t support HTML5

የበረራ ቡድን ማገዱን የኢትዮጵያ አየር መንገድ አስታወቀ