የአውሮፓ ህብረት የማሊውን የወታደራዊ ሥልጠና ተልዕኮውን እንደሚያቆም አስታወቀ

  • ቪኦኤ ዜና
ፎቶ ፋይል - የተባበሩት መንግሥታት የሰላም አስከባሪ ተልዕኮ ወታደሮች በጋኦ፣ ማሊ

ፎቶ ፋይል - የተባበሩት መንግሥታት የሰላም አስከባሪ ተልዕኮ ወታደሮች በጋኦ፣ ማሊ

አህጉራዊው ህብረት የማሊ ወታደሮችን የማሰልጠን ተልዕኮውን ለማቆም ትናንት ሰኞ ውሳኔ ላይ መድረሱን አንድ ከፍተኛ የህብረቱ ዲፕሎማት ገልጸዋል። አክለውም ነገር ግን ከሳህል አካባቢ በጠቅላላ እንወጣለን ማለት አይደለም ብለዋል።

የአውሮፓ ህብረት የውጭ ፖሊሲ ኃላፊው ጆሴፕ ቦሬል ባካሄዱት ጋዜጣዊ ጉባዔ የማሊን የጦር ኃይሎች እና ብሄራዊ ዘብ ማሰልጠኛ ስምሪታችን ይቆማል።

ነገር ግን የሳህል አካባቢ ነገር በቃን ማለታችን ግን አይደለም፣ ቅድሚያ ትኩረት የምንሰጠው አካባቢ ነው፤ እንድያውም ተጨማሪ ድጋፍ ለመስጠት እንፈልጋለን ብለዋል።

ቦሬል በማሊ ጉዳይ ለመነጋገር የተካሄደውን የህብረቱን አባል ሀገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ ከመሩ በኋላ በሰጡት ቃል ውሳኔው ላይ የተደረሰው ማሊ ውስጥ የደረሱት ክስተቶች የሩሲያው የግል ወታደራዊ ኩባኒያ ቫግነር ግሩፕ በሀገሪቱ ጣልቃ እንደማይገባ ምንም ዓይነት ዋስትና ባለማግኘታችን ተገድደን ነው ሲሉ አስረድተዋል።

ፈረንሳይ እና ሌሎችም ሀገሮች ቫግነር ግሩፕ ተዋጊዎቹን ማሊ ውስጥ በጦር ሰራዊትነት አሰማርቷል ብለዋል። የማሊ ወታደሮች እና የቫግነር ቅጥር ተዋጊዎች ሞራ በምትባል የማሊ መንደር ከሁለት መቶ በላይ ሰላማዊ ሰዎች ገድለዋል የሚሉት ሪፖርቶች እንዳሳሰቧት ባለፈው ሳምንት ፈረንሳይ ማስታወቋ እና ወታደሮችዋን እንደምታስወጣም ገልጻለች።

የጀርመን ወታደሮች መቆየትም ጉዳይም ጥያቄ ውስጥ የገባ ሲሆን የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አናሌና ቤርቦክ ከማሊ ወታደራዊ አገዛዝ በዚህ ሳምንት ውስጥ እንደሚነጋገሩ ተዘግቧል።

የማሊ ወታደሮች እና ባዕዳን ተዋጊዎች በምስራቅ ማሊ ሞራ መንደር ውስጥ ባለፈው ወር ሦስት መቶ ሲቪሎችን እንደገደሉ ሂዩማን ራይትስ ዋች ባወጣው ሪፖርት ማስታወቁ ይታወሳል።