ቡርኪና ፋሶ ጋዜጠኛ ለመግደል የዛተ ተጠርጣሪ አሰረች

  • ቪኦኤ ዜና

ኒውተን አህመድ ቤሪን

ቡርኪና ፋሶ ውስጥ አንድ ታዋቂ ጋዜጠኛ ለመግደል በማኅበራዊ መገናኛ ላይ ዝቷል የተባለን ሰው በኢንተርኔት የሚፈፀሙ ወንጀሎች ተከታታይ ፖሊስ ይዞ ማሰሩን የሀገሪቱ ባለሥልጣናት ገለፁ።

የፖሊስ ፀረ-ሳይበር ወንጀሎች ብሪጌድ ትናንት ሰኞ ባወጣው መግለጫ "በንግድ ሥራ የሚተዳደር የሰላሳ አምስት ዓመት ዕድሜ ያለው ሰው የኒውተን አህመድ ቤሪን ስም የሚያጎድፍ ጥቃት እና የንብረት ውድመት እንዲፈፀምበት የሚቀሰቀስ መልዕክት በማኅበራዊ መገናኛ ላይ አሠራጭቷል" ብሏል።

ተጠርጣሪው በዋትስአፕ ላይ ባሠራጨው መልዕክት ጋዜጠኛውን "መኖር የማይገባው አሸባሪ" ብሎ "ሂዱና ቤቱን አቃጥሉ" በማለት ጥቃት እንዳነሳሳበት ፖሊስ አመልክቷል።

(እአአ) በ1980ዎቹ ዓመታት የመንግሥት ቴሌቭዥን ስመ ጥር ጋዜጠኛና የአንድ መርማሪ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ በነበረው ኒውተን ቤሪ ላይ ዛቻውና ቅስቀሳው ለምን እንደተካሄደበት ግልፅ የሆነ ነገር የለም።

ይሁን እንጂ ጋዜጠኛው የቡርኪና ፋሶ መንግሥት አክራሪ እስላማዊ አማፂያንን በመዋጋት የሚረዱትን ሩሲያውያን ቅጥር ተዋጊዎች ለማስገባት መዋዋሉን በአንድ የግል ቴሌቭዥን ላይ ከነቀፈ ወዲህ በአፍቃሪ ሩሲያ ወገኖች እየተወገዘ መሆኑን ኤኤፍፒ በዘገባው አውስቷል።