ቦሪስ ጆንሰን መልቀቃቸውን አሳወቁ

የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰ

የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰ ሥልጣናቸውን ዛሬ በፍቃዳቸው መልቀቃቸውን አሳውቀዋል።

የጆንሰን ሥልጣን የመልቀቅ ጭምጭምታ ከማለዳው አንስቶ ሲሰማ የነበረው ሃምሳ የሚሆኑ ሚኒስትሮቻቸውና ከፍተኛ ባለሥልጣኖች የስንብት ጥያቄዎችን እያቀረቡ ሥራቸውን ከለቀቁ በኋላ ነው።

መንግሥታቸው በበዙ የሥነምግባር ግድፈቶች የተከሰሰ ቢሆንም ጆንሰን እስከ ትናንት ረቡዕ ሥራቸው ላይ ለመቆየት አበክረው ሲሟገቱ እንደነበር ተነግሯል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚለቅቁ ይናገሩ እንጂ አዲስ መሪ የመንግሥቱን ሥራዎች እስኪረከብ በሞግዚትነት እንደሚቆዩ ገልፀዋል።

የመጀመሪያዎቹ ሁለት ከፍተኛ ሹማምንት፤ የገንዘብ ሚኒስትራቸው ሪሺ ሱናክና የጤና ሚኒስትሩ ሳጂድ ጃቪድ ትናንት ተከታትለው ሥልጣናቸውን ከለቀቁ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዓመታዊው የጥያቄና መልስ መርኃግብር ፓርላማው ውስጥ ፊት ሲቀርቡ በተሰሙባቸው ክሦች የተቆጡት እንደራሴዎች በብርቱ ጥያቄዎች አጣድፈዋቸዋል።

ጆንሰንን ሚኒስትሮቻቸው እየተዋቸው የለቀቁት ለንደን በሚገኝ አንድ ክለብ ውስጥ በመጠጥ ኃይል ተገፋፍተው ሁለት ወንዶችን ያላግባብ ጎንትለዋል የሚል ክሥ የሚሰማባቸውን ወግ አጥባቂ የምክር ቤት አባል ክሪስ ፒንቸርን ቁልፍ በሆነ የፓርቲ ኃላፊነት ላይ ከሾሟቸው በኋላ መሆኑ ተነግሯል።

የጆንሰን ስለጉዳዩ እንደማያውቁ ረዳቶቻቸው ቀደም ሲል ለጋዜጠኞች ገልፀው የነበረ ቢሆንም “በመንግሥቱ ውስጥ ለአንድም የቅሌት አድራጎት ቦታ የለም” ይሚል ጠንካራ አቋም ይዘዋል።

ሚስተር ጆንሰን ከዚህ በፊትም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ፅህፈት ቤት ውስጥ በተካሄዱና የኮቪድ-19 መከላከያ መመሪያዎችን እራሳቸው ጭምር ጥሰው እንደተገኙባቸው በተነገረ የፈንጠዝያ ስብሰባዎችም ሲከሰሱ እንደነበር ተዘግቧል።

/የዚህ ዜና ይዘት ፈጥኖ ሊለወጥ ይችላል/