አንጎላ ረቡዕ ምርጫ ላይ ነች

  • ቪኦኤ ዜና

የኡኒታ መሪ አዳልቤርቶ ኮስታ ጁኒየር

ላለፉት 47 ዓመታት ሥልጣን ላይ የኖረው የአንጎላ ነፃነት ህዝባዊ ንቅናቄ ወይም ኤምፒኤልኤ እና በወጣቶች ዘንድ ተቀባይነቱ እየጨመረ የመጣው የተቃዋሚው ኡኒታ ፓርቲ የተፋጠጡበት የአንጎላ አጠቃላይ ምርጫ ነገ፤ ረቡዕ ይካሄዳል።

ከባድ ፉክክር ይታይበታል ለተባለው ለዚህ ምርጫ እየተወዳደሩ ያሉት እጩዎች ዘመቻቸውን ዛሬ አጠቃልለዋል።

ኤምፒኤልኤ አንጎላ ከፖርቹጋል ቅኝ ነፃ ከወጣችበት ከ1967 ዓ.ም. አንስቶ መርቷታል።

የከርሰ ምድር ዘይት በማውጣት በአፍሪካ ሁለተኛ በሆነችው አንጎላ የተፈጥሮ ሃብቷ ሁሉንም ተጠቃሚ አላደረገም በሚል በገዢው ፓርቲ ላይ ከፍተኛ ቅሬታ እያደገ በመምጣቱ የረዥም ጊዜ ተቃዋሚው የአንጎላ ነፃነት ብሄራዊ ህብረት ወይም ኡኒታ እየተጠናከረ መምጣቱ ይነገራል።

በሺሆች የሚቆጠሩ የኡኒታ ደጋፊዎች ለመጨረሻ የምርጫ ዘመቻ ቀናቸው ዛሬ የፓርቲውን መለያ ቀለም ያላቸውን አልባሳት ለብሰው ዋና ከተማዪቱ ሉዋንዳ ውስጥ ተሰባስበው ነበር።

የኡኒታ መሪ አዳልቤርቶ ኮስታ ጁኒየር ለደጋፊዎቻቸው ባደረጉት ንግግር ሲያደርጉ ለፖለቲካ ለውጥ አስፈላጊነት አፅንኦት ሰጥተዋል።

አፍሮባሮሜትር የሚባለው የህዝብ አመለካከት ቃኚ ተቋም ባለፈው ግንቦት ባካሄደው ግምገማ አንጎላዊያን ለኡኒታ የሚሰጡት ድጋፍ የዛሬ ሦስት ዓመት ከነበረው 13 ከመቶ ዘንድሮ ወደ 22 ከመቶ ማሻቀቡን ይፋ አድርጓል።

ነገር ግን ከኤምፒኤልኤ በሰባት ነጥብ ያነሰ ስሆን ከድምፅ ሰጭው ግማሹ ማንን እንደሚመርጡ ገና ለመወሰናቸውን ሮይተርስ አመልክቷል።

በኤምፒኤልኤ የምረጡኝ ዘመቻውን ከትናንት በስተያ ቅዳሜ ሲያጠቃልል የአሁኑ ፕሬዚዳንት ጆአኦ ሎሬንሶ ግን ትናንት በሴቶች መብቶች ላይ ባተኮረ ዝግጅት ላይ ተገኝተዋል።

በአብዛኛው በኤምፒኤልኤ ቁጥጥር ሥር ያለው የምርጫ ኮሚሽን ሂደቱ ፍትሃዊና ግልፅ ይሆናል ቢልም ‘ምርጫው ሊጭበረበር ይችላል’ የሚል ሥጋት በመኖሩ ደጋፊዎቹ ድምፅ ከሰጡ በኋላ እዚያው አካባቢ ቆይተው ሂደቱን እንዲከታተሉ ኡኒታ ጥሪ አድርጓል።

የፀጥታ ጥናቶች ተቋም የሚባል ድርጅት ባወጣው ሪፖርት ኤምፒኤልኤ ምርጫውን ካጭበረበረ ብጥብጥ ሊከተል ይችላል ሲል አስጠንቅቋል።