ዛሬ በአዲስ አበባ በተጀመረው 38ኛው የመሪዎች ጉባኤ ላይ "የማካካሻ ፍትሕ" ጥያቄ ቀዳሚ አጀንዳ ሆኗል፡፡
በመክፈቻው ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ የማካካሻ ጥያቄው “የርዳታ ሳሆን የፍትሕ ጥያቄ ነው” ብለዋል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዥ ደግሞ “ለማካካሻ ፍትሕ ማዕቀፎች ጊዜው አሁን ነው” ሲሉ ጥያቄው መልስ እንዲያገኝ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
38ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ዛሬ ቅዳሜ የካቲት 8 ቀን በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው የኅብረቱ ዋና አዳራሽ ሲጀመር፣ እንደ የባሪያ ፍንገላ፣ ቅኝ ግዛት እና አፓርታይድ ላሉ በአህጉሪቱ ለተፈጸሙ ቀደምት ኢ-ፍትሐዊ ተግባራት የማካካሻ ፍትሕ ጥያቄ ማቅረብን ዋነኛ አጀንዳው አድርጓል፡፡
"የማካካሻ ፍትሕ ለአፍሪካውያንና ዘርዓ-አፍሪካውያን” በሚል መሪ ቃል በተጀመረው በዚህ ጉባኤ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ ጥያቄው ፍትሕን የመሻት ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡
“የማካካሻ ጥያቄው የበጎ አድራጎት ወይም የገንዘብ ርዳታ ጥያቄ አይደለም" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ስለ ፍትሕ ነው። የሚሊዮኖችን ክብር የመመለስ እና ጥልቅ የሆነ የድህነት፣ የመበላለጥ እና የአድሎ ጠባሳን መፈወስን የሚጠይቅ ነው። በሀብቶቻችን እና ዕድሎቻችን ላይ የሚፈጸመው ስልታዊ ብዝበዛን እንዲቆም ይጠይቃል። በተጨማሪም በአህጉሪቱ ውስጥ ባሉ ማኅበረሰቦች ላይ የተፈጠሩ በደሎችን ለማረም ድፍረት የተሞላበት ርምጃ የሚወሰድበት የለውጥ ሂደት እንዲኖር የሚጠይቅ ነው። ከሁሉም በላይ፣ የማካካሻ ጥሪው የእያንዳንዱን ሰው እኩልነት ለማረጋገጥ ቃላትን ብቻ ሳይሆን ተጨባጭ ድርጊቶችን ይጠይቃል።” ብለዋል።
በኅብረቱ የመሪዎች ጉባዔ መክፈቻ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዥም፣ የኅብረቱ የካሳ ጥያቄ አግባብ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
“አፍሪካ የሁለት ከባድ እና የተወሳሰቡ ኢፍትሃዊ ድርጊቶች ሰለባ መሆኗን ዓለም መዘንጋት የለበትም።እነዚህም፣ የቅኝ ግዛት እና የአትላንቲክ የባሪያ ንግድ ከፍተኛ ተጽዕኖዎች ናቸው። የእነዚህ ድርጊቶች ሥረ መሰረት በመቶዎች የሚቆጠሩ ዓመታትን ያስቆጠረ ነው፡፡ መራራ ፍሬው ግን አፍሪካውያንን እና ዘርዓ-አፍሪካውያንን እስከ ዛሬ ድረስ እየጎዳ ነው፡፡ ከቅኝ ግዛት መላቀቅ በራሱ መድኃኒት አይደለም። የፖለቲካ ነፃነት፣ ሀገሮችን በብዝበዛ ላይ ከተመሠረቱ መዋቅሮች እና ለበርካታ ዐስርት ዓመታት ከዘለቀው የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊ እና ተቋማዊ የኢንቨስትመንት እጥረት ነፃ አላደረገም። ለማካካሻ ፍትህ ማዕቀፎች ጊዜው አሁን ነው።” ብለዋል።
SEE ALSO: የጅቡቲው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ኾኑየኅብረቱ አባል ሀገራት መሪዎች በሁለት ቀናት በሚያደርጉት ውይይት በዚሁ የማካካሻ ፍትኅ ጉዳይ ላይ ከፍተኛ ትኩረት እንደሚያደርጉ፣ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበርነት ስፍራን ከሞሪታኒያው ፕሬዝደንት ዛሬ የተረከቡት የአንጎላው አቻቸው ዡዋ ሎሬንሶ ተናግረዋል፡፡
“በዚህ ጉባኤ በብዙ ጉዳዮች ላይ ውይይት ይደረጋል" ያሉት ዡዋ ሎሬንሶ "ነገር ግን ለአህጉራችን በጣም አስፈላጊ የሆኑት የአፍሪካ ህብረት የስራ ማዕቀፍ እና ለዚህ ዓመት በመሪ ሃሳብነት የተመረጠውን፣ ለአፍሪካ እና ለትውልደ አፍሪካውያን የማካካሻ ፍትህን ተግባራዊ እንዲሆን የማድረግ ጉዳይ ዋናዎቹ ናቸው” ብለዋል።
የማካካሻ ፍትሕ ጥያቄውን በተመለከተ አስተያየታቸውን የሰጡን የአፍሪካ ጉዳዮች ከፍተኛ ተመራማሪና የፖለቲካ ተንታኝ ዶ/ር ሄኖክ ጌታቸው፣ ጠያቄው አሁን ዋና አጀንዳ ቢሆንም ከከአፍሪካ አንድነት ድርጅት ጀምሮ በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲነሳ የነበረ ነው ብለዋል፡፡
SEE ALSO: የአንጎላውን ፕሬዝደንት ዡዋ ሎሬንሶ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር ኾኑከማካካሻ ፍትሕ በተጨማሪ፣ የአኅጉሪቱ ፈተና ኾኖ የቀጠለውን የሰላምና ፀጥታ እጦት ጨምሮ፣ የወጣቶች ጥያቄ፣ ትምህርትና ጤናን የመሳሰሉ ጉዳዮችም የውይይት አጀንዳዎች እንደሚሆኑም ተገልጿል፡፡
ተሰናባቹ የኅብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ መሃማት፣ በአኅጉሪቱ የቀጠሉ ግጭቶች ከሌሎች ተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ ቀውሶች ጋር ተዳምረው በአብዛኛው የኅብረቱ አባል አገራት ወትሮውንም የነበረውን የደኅንነት ምግብ የጤና እና መሰል ችግሮች እያባባሰ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡