ከፍልስጤም የነፃነት ድርጅት (ፒ ኤል ኦ) ተወካዮች ጋራ ዛሬ የተገናኙት የግብጹ የውጪ ጉዳይ ምኒስትር የፍልስጤማውያን ራስ ገዝ አስተዳደር እንዲጠናከርና ፍልስጤማውያን በአንድነት እንዲቆሙ ጥሪ አድርገዋል።
በውይይቱ ወቅት የውጪ ጉዳይ ምኒስትር ባድር አብደላቲ ለፍልስጤማውያን ራስ ገዝ አስተዳደር ሃገራቸው ያላትን ድጋፍ እንደገለጹ ከቢሯቸው የወጣው መግለጫ አመልክቷል።
በተጨማሪም ፍልስጤማውያንን ከመሬታቸው ላይ ለማፈናቀል ያለም ማንኛውም ዕቅድ ግብጽ እንደምትቃወም ማስታወቃቸው ተመልክቷል።
ግብጽ ባለፈው ወር ፋታህ እና ሐማስ በተሰኙት ፍልስጤማውያን ቡድኖች መካከል ጋዛ ከጦርነቱ በኋላ በፍልስጤማውያን ራስ ገዝ አስተዳደር ቁጥጥር ሥር በሚሆንበት ሁኔታ ላይ ውይይት አስተናግዳ ነበር።
በእስራኤል በተያዘው ዌስት ባንክ የተወሰነውን ክፍል የሚያስተዳድረው ፋታህ፣ በፍልስጤማውያን ራስ ገዝ አስተዳደርም ሆነ ፍልስጤማውያንን እንደሚወክል ዓለም አቀፍ እውቅና ባለው ፒ ኤል ኦ ላይ ተጽእኖ እንዳለው ይነገራል።
ሐማስ በእ.አ.አ 2007 ጋዛን ከተቆጣጠረ ወዲህ ፋታህ ከጋዛ እንዲገለል ተደርጓል።