በአሜሪካ ምክር ቤት የምርጫ  ውጤት ማረጋገጫ ሥነ ሥርዓት ተካሄደ

  • ቪኦኤ ዜና

በዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት ዶናልድ ትረምፕ በፕሬዝደንታዊ ምርጫ ማሸነፋቸውን ማረጋገጫ ሥነ ሥርዓት ዛሬ ተካሂዷል።

ከ50 ግዛቶች የተላኩትን የድምጽ ቆጠራ ውጤቶችን የማረጋገጡን ሥነ ሥርዓት የመምራት ኅላፊነት የሃገሪቱ ምክትል ፕሬዝደንት በመሆኑ፣ በፕሬዝደንታዊ ምርጫው የተሸነፉት ካመላ ሄሪስ የዶናልድ ትረምፕን ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን፣ የራሳቸውንም መሸነፍ ማረጋገጫ ሰጥተዋል።

በጋራ ም/ቤቱ የሚካሄደው የድምጽ ቆጠራ ውጤት ማረጋገጫ ሥነ ሥርዓት በአሜሪካ የምርጫ ሂደት ለረጅም ጊዜ ሲካሄድ የቆየ ሥነ ሥርዓት ነው። ሆኖም የዛሬው የምርጫ ውጤት ማረጋገጫ ሥነ ሥርዓት የሚካሄደው ከአራት ዓመታት በፊት ተመሳሳይ ሥነ ሥርዓት በሚካሄድበት ወቅት በምርጫው የተሸነፉት ዶናልድ ትረምፕ ደጋፊዎች ሥነ ሥርዓቱን ለማስቆም በምክር ቤቱ ላይ ጥቃት መፈጸማቸው በሚታወስበት ሁኔታ ውስጥ ነው።

በወቅቱ በተፈጸመው ጥቃት 140 የፖሊስ አባላት ጉዳት ሲደርስባቸው፣ አንዲት ግለሰብ ከፖሊስ በተተኮሰ ጥይት ሕይወቷ አልፏል። ሌሎች ቢያንስ አራት ሰዎች ደግሞ ከጥቃቱ ጋራ በተያያዘ ሕይወታቸውን አጥተዋል።

ምክትል ካመላ ሄሪስ በምርጫው መሸነፋቸውን ሲያምኑ ፕሬዝደንት ጆ ባይደንም ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር እንደሚካሄድ በማስታወቃቸው የዛሬው ሥነ ሥርዓት በሠላም ተጠናቋል።

ከአራት ዓመታት በፊት በጥቃቱ ተሳትፈው በፍርድ ቤት ጥፋተኛ የተባሉ ግለሰቦች ደጋፊ የሆኑ ሰዎች ትላንት ዕሁድ ዋሽንግተን ዲሲ በሚገኝ አንድ እሥር ቤት ደጃፍ ላይ የሻማ ማብራት ሥነ ሥርዓት አድርገዋል።

በጥቃቱ 1 ሺሕ 500 የሚሆኑ ሰዎች በፍርድ ቤት ጥፋተኛ ተብለዋል። ዶናልድ ትረምፕ ሥልጣኑን እንደተረከቡ በይቅርታ እንደሚያስፈቷቸው አስታውቀዋል።