የዩናይትድ ስቴትሷ ግዛት ፖርቶ ሪኮ 1ነጥብ 3 ሚሊዮን የሚደርሱ ነዋሪዎችዋ መብራት በመቋረጡ አዲሱን የአውሮፓውያን ዓመት በጨለማ ለመቀበል እየተዘጋጁ ነው፡፡
ባለሥልጣናት የተቋረጠውን የመብራት አገልግሎት ለመመለስ እስከ ሁለት ቀናት ሊፈጅ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
የኃይል መቋረጡ የተፈጠረው ዛሬ ማክሰኞ ማለዳው ላይ በተከሰተ የኤሌክትሪክ መስመር ብልሽት ምክንያት ነው፡፡
ጄኔሬተሮችን ለመጠቀም አቅሙ ካላቸው በስተቀር፣ የደሴቲቱ አብዛኛው ክፍል ፀጥታ እና ጨለማ ውስጥ ወድቋል።
ችግሩ የተከሰተው ከመሬት በታች ባለው የኤሌክትሪክ መስመር ውስጥ መሆኑን የገለጸው ሉማ ኢነርጂ የተባለው የመብራት ኃይል ድርጅት መንስኤውን እያጣራ መሆኑን ገልጿል፡፡ በተቻለ ፍጥነትን የተቋረጠውን ኅይል ወደ ነበረበት ለመመለስ እየሠራ መሆኑንም ድርጅቱ አስታውቋል።
ፖርቶ ሪኮ የኃይል መሠረተ ልማቶቿ ወትሮውኑም ደካማና ጥገና የጎደላቸው ቢሆንም፣ እኤአ በ2017 ሄሪኬን ማሪያ የሚል ስያሜ በተሰጠው ከባድ አውሎ ነፋስና ዝናብ ከተመታች ወዲህ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ወድቃለች፡፡