የደቡብ ኮሪያ ፕሬዝዳንት ዩን የእሥር ማዘዣ ወጣባቸው

  • ቪኦኤ ዜና

የደቡብ ኮሪያ ፕሬዝዳንት ዩን ሱክ ዮል ደቡብ ኮሪያ፣ እአአ ታኅሣሥ 7/2024

የደቡብ ኮሪያ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዩን ሱክ ዮል ላይ የተጠየቀውን የእሥር ማዘዣ ዛሬ ማክሰኞ አጽድቋል፡፡

ታኅሣሥ ወር ውስጥ የወጣውንና በአጭሩ የተቀጨውን ወታደራዊ ሕግ ለማወጅ ባደረጉት ሙከራ ከሥልጣን እንዲነሱ የተወሰነባቸው ፕሬዝዳንት ዩን ዐመጽ የማስነሳት ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡

የሶል ምዕራብ አውራጃ ፍርድ ቤት የእሥር ማዘዣውን ያወጣው ዛሬ ማክሰኞ መሆኑን የዘገቡት የሀገሪቱ ብዙኅን መገናኛ፣ "በደቡብ ኮሪያ በሥልጣን ላይ እያሉ የእሥር ማዘዣ የወጣባቸው የመጀመሪያው ፕሬዝዳንት ናቸው" ብለዋል፡፡

ዩን ሕገ መንግሥታዊው ፍርድ ቤት ባደረገው ማጣራት ፕሬዝዳንታዊ ሥልጣናቸው ተገፍፎ ከኃላፊነት እንዲነሱ የተወሰነባቸው በታኅሣሥ ወር አጋማሽ ላይ ነበር፡፡

ዩን ከሥልጣን እንዲነሱ ካስወሰነባቸው ክስ በተጨማሪ አመፅ በመቀስቀስ እና እና ሥልጣንን ያለአግባብ በመጠቀም በመንግሥት ጥምር የመርማሪ ቡድን ምርመራ እየተካሄደባቸው ነው።

ፕሬዝዳንት ዩን የተከሰሱበትን ጉዳይ ቀርበው እንዲያስረዱ የተላኩላቸውን ሦስት የተለያዩ መጥሪያዎች ችላ በማለታቸው፣ ዛሬ ማክሰኞ የፍርድ ቤት እሥር ማዘዣ እንዲወጣባቸው ማድረጉ ተገልጿል፡፡

የዩን ጠበቃ የእሥር ማዘዣው “ሕገ ወጥ ነው” በማለት ሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤት ትእዛዙን እንዲያስቆመው ጠይቀዋል፡፡

የእሥር ማዘዣው እስከ መጭው ሰኞ ድረስ ይሠራል፡፡ ባለሥልጣናት እሥሩን መች እና በምን ሁኔታ ለማስፈጸም እንደሚሞክሩ ግልጽ አለመሆኑ በዘገባው ተጠቅሷል፡፡

የፕሬዝዳንቱ ደኅንነት ጠባቂዎች ወደ ፕሬዝዳንታዊ ጽሕፈት ቤት ግቢ፣ ወይም ወደ የዩን የኦፊሴል መኖሪያ ቤት፣ የፍርድ ቤት ብርበራ ትዕዛዝ ይዘው የመጡትን መርማሪዎች የደኅንነት እና ወታደራዊ ጉዳዮችን በመጥቀስ እስካሁን ድረስ እንዳይገቡ ከልክለዋል፡፡

የደቡብ ኮሪያ ገዥው ወግ አጥባቂ ፒፕል ፓወር ፓርቲ ተጠባባቂ ኃላፊ ዛሬ ማክሰኞ በሰጡት አስተያየት የእሥር ማዘዣውን “እጅግ የሚያሳዝን” ብለውታል።