ፈረንሣይ ሶሪያ በሚገኙ እስላማዊ መንግሥት ታጣቂዎች ላይ የአየር ድብደባ መፈጸሟን ዛሬ ማክሰኞ አስታወቀች።
የፈረንሣይ የመከላከያ ሚኒስትር ሴባስቲያ ለኮርኑ ኤክስ ላይ ባሰፈሩት ጹሑፍ ፣ ጥቃቱ የተፈጸመው ከትላንት በስቲያ እሑድ መሆኑን ቢያስታውቁም፣ ሶሪያ ውስጥ የት ቦታ እንደተፈጸመ ግን አልገለጹም።
የፈረንሣይ ጥቃት የተፈጸመው አማፂያኑ የሶሪያን ፕሬዝዳንት ባሻር አል አሳድን ከሥልጣን ካባረሩ በኋላ በነበሩት ሳምንታት ውስጥ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በእስላማዊ መንግሥት ኢላማዎች ላይ ያደረሰቻችውን በርካታ ጥቃቶች ተከትሎ ነው።
የእስላማዊ መንግሥት ታጣቂዎች በምሥራቅ ሶሪያ እና በምዕራብ ኢራቅ ሰፋፊ አካባቢዎችን የተቆጣጠሩት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2014 ነው፡፡ ይህ ርምጃቸው በዩናይትድ ስቴትስ የተመራውን ጥምረት ያካተተ ቡድኑን የማጥፋት ዓለም አቀፍ ምላሽ አስከትሏል፡፡
ታጣቂዎቹ በአንድ ወቅት ይቆጣጠሩት ከነበረው ግዛት አብዛኛውን ቢያጡም አሁን ድረስ ሶሪያ ውስጥ ይገኛሉ።
የምዕራቡ ዓለም ወታደራዊ ጥቃቶች የተፈጸሙት ከአሳድ መንግሥት ውድቀት በኋላ ስለ ወደፊቱ የሶሪያ ፖለቲካዊ እና ደኅንነት ጥያቄዎች እየተነሱ ባሉበት በአሁኑ ወቅት ነው።
አሳድ ሀገሪቱን ለቀው እንዲወጡ ያደረገውን ፈጣን ግስጋሴ የመሩት ሁሉም አማፂ ቡድኖች ፈርሰው በሶሪያ ጦር ሥር እንደሚዋሃዱ አስታውቀዋል።
አዲሶቹ የሶሪያ ባለሥልጣናት ሙርሃፍ አቡ ቃስራን የመከላከያ ሚኒስትር አድርገው መምረጣቸውን ዛሬ ማክሰኞ አስታውቀዋል።
ቃስራ አሳድን ከሥልጣን ያስወገዱትን አማፂያን በመራው ሃያት ታህሪር አል ሻም ቡድን ውስጥ ግንባር ቀደም መሪ ነበሩ።