በሲዳማ ብሔራዊ ክልል ፣ ምስራቃዊ ሲዳማ ዞን በተከሰተ የመኪና አደጋ 71 ሰዎች መሞታቸውን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ።
የዞኑ አስተዳዳሪ ማቴ መንገሻ (ዶ/ር) አደጋው የተከሰተው ከሀዋሳ 125 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ቦና ወረዳ- ገላና ወንዝ ተብሎ በሚጠራዉ አከባቢ መሆኑን ለአሜሪካ ድምጽ ተናግረዋል ። 68 ወንዶች እና 3 ሴቶች በአጠቃላይ 71 ሰዎች ወድያወኑ መሞታቸው መረጋገጡን አስታውቀዋል።
የቦና ሆስፒታል ስራ አስኪያጂ አቶ አሸናፊ ብልሶ ከሟቾች በተጨማሪ ፣ 4 ሰዎች ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ሆስፒታሉ መጥተው ህክምና እያገኙ መኾናቸውን ለአሜሪካ ድምጽ ተናግረዋል።
አንድ ተጎጂ ደግሞ ከፍ ላለ ህክምና ወደ ሀዋሳ ሪፌራል ሆስፒታል መላካቸውም ተገልጿል።
የዞኑ አስተዳዳሪ ማቴ መንገሻ (ዶ/ር) ተሳፋሪዎችን ጭኖ ሲጓዝ የነበረ ኤፍ ኤስ አር አይሱዙ የተባለ የጭነት መኪና መንገዱንን ስቶ ፣ በገላና ወንዝ ላይ ከሚገኘው መሻገሪያ ድልድይ ወደ ወንዙ በመውርወሩ ምክንያት አደጋው እንደተከሰተ አብራርተዋል።
የአደጋው ሰለባ የኾኑት ከአንድ የሰርግ ስነስርዓት እና በቡና ሳይት ስራ ላይ ቆይተዉ ሲመለሱ የነበሩ የአንድ አከባቢ ወጣቶች መሆናቸውን አስተዳዳሪው አክለው ተናግረዋል ።