በትግራይ ክልል ፣የመንግስታዊው ትግራይ ቴሌቭዥን ጋዜጠኞች ቡድን አባላት ከሰዓታት "እስር " በኃላ በዛሬው ዕለት መለቀቃቸው ተሰምቷል።
የክልሉ መንግስት ንብረት የሆነው ቴሌቭዥን ጣቢያ ጋዜጠኞች ቡድን አባላት ፣ ለእስር በተዳረጉበት ወቅት በሰሜን ምዕራብ ትግራይ በሚገኝ የወርቅ ማዕድን ማውጫ ላይ የምርመራ ዘገባ እየሰሩ እንደነበር ታውቋል።
ቴሌቭዥን ጣቢያው ጋዜጠኞቹ በአስገደ ወረዳ ፣ በሚይሊ ቀበሌ ተገኝተው ለወርቅ ማዕድን ማውጣት አገልግሎት ላይ የሚውሉ ኬሚካሎች የፈጠሩትን ጉዳት በተመለከተ ምርመራ እያደረጉ እንደነበረ አረጋግጧል።
ለደህንነት ሲባል ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የጣቢያው የቅርብ ምንጮች ለቪኦኤ እንደገለፁት አንድ ጋዜጠኛ፣ አንድ የካሜራ ባለሙያ እና ሾፌራቸው ለእስር ተዳርገዋል።
ቆየት ብሎ ከቴሌቭዥን ጣቢያው የወጣው መግለጫ የጋዜጠኛ ቡድኑ አባላት መፈታታቸውን አረጋግጧል።
ከታሰሩት ጋዜጠኞች መካከል አንዱ የሆነው እና "ከ 7 ሰዓታት" እስር በኃላ እንደተለቀቀ የተናገረው ተስፋዝጊ ዓስበይ ፣ የደንብ ልብስ ያልለበሱ ሰዎች በቁጥጥር ስር እንዳዋሏቸው እና ሚይሊ ውስጥ በሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ያሰሯቸው አካላት የአካባቢው የጸጥታ ኃይሎች መሆናቸውን ቆይቶ መረዳቱን ለአሜሪካ ድምጽ ተናግሯል።
ተስፋዝጊ የአካባቢው ባለስልጣናት እሱ እና ባልደረቦቹን እንዳስፈቷቸውንም አክሎ ገልጿል።
የሰሜን ምዕራብ ትግራይ የጸጥታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ተስፋይ አባዲ በአካባቢው የነበሩ የጸጥታ አካላት ጋዜጠኞችን በቁጥጥር ስር ያዋሏቸው " በአካባቢው ቀረፃ ለማካሔድ የሚያስችል የፍቃድ ደብዳቤ ስላልያዙ ነው " ፣ ሲሉ ለአሜሪካ ድምጽ ተናግረዋል።