በምስራቅ ጎጃም ዞን ደብረ ኤልያስ ወረዳ ሁለት ሴት የመንገድ ትራንስፖርት ሠራተኞች "ፋኖ ናቸው" በተባሉ ታጣቂዎች መገደላቸውን የወረዳው አስተዳዳሪ አስታወቁ።
ወረዳው ከአንድ ዓመት በላይ በፋኖ ቁጥጥር ስር እንደነበር ለአሜሪካ ድምፅ የተናገሩት የወረዳው አስተዳዳሪ ሀብታሙ እሱባለው ፣ የመንግሥት ኃይሎች ታጣቂዎቹን ከአካባቢው በማስለቀቃቸው ካለፈው ሳምንት ጀምሮ የመንግሥት ሥራ መጀመሩን ተናግረዋል። ሥራ በመጀመሩ ወደ ወረዳው እየተመለሱ ነበር የተባሉ የመንገድ ትራንስፖርት ሠራተኞችን "የፋኖ ታጣቂዎች" ናቸው የተባሉ ታጣቂዎች ከተሳፈሩበት የጭነት መኪና አስወርደው ገድለዋቸዋል" ሲሉ አስተዳዳሪው ተናግረዋል።
Your browser doesn’t support HTML5
የአንደኛዋ ሟች መልካም ተስፋዬ የቅርብ ዘመድ መኾናቸውን የነገሩን ለደኅንነታቸው በመስጋት ስማቸውን እንዳንጠቅስ የጠየቁ ግለሰብ አስከሬን መረከባቸውንና ለቀብር ወደ ቢቡኝ ወረዳ መላኩን ገልጸው፣ አካባቢው ላይ ባለው የጸጥታ ችግር ምክኒያት እርሳቸው መቅበር አለመቻላቸውን ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።
ተፈፀመ ስለተባለው ጥቃት በአካባቢው ከሚንቀሳቀሰው የአማራ ፋኖ በጎጃም ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም።
በአሜሪካ ድምጽ ዘጋቢዎች የተጠናቀረውን ዘገባ ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ፡፡