ባይደን በዩክሬን እና ሶሪያ ጉዳይ ከቡድን 7 ሀገራት ጋር ተነጋገሩ

በአውሮፓዊያኑ ታህሳስ 13 .2024 የተነሳው ምስል በቼርኒሂቭ ክልል በሩስያ ሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት የደረሰባቸው ህንጻዎች በእሳት ሲጋዩ ያሳያል ።

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ኪየቭ ከሩሲያ ጋር እያደረገች ላለችው ውጊያ የሚሆን ድጋፍን ለማረጋገጥ ያለመ የርቀት መገናኛ ስብሰባ ከቡድን 7 መሪዎች ጋር በትናንትናው ዕለት አከናውነዋል። የአሁኑ ስብሰባ የተደረገው ለዩክሬን በሚሰጠው ድጋፍ ዙሪያ ትችት የሚያሰሙት ተመራጩ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ፣ ስልጣን ሊረከቡ ስድስት ሳምንታት ብቻ በቀሩበት ወቅት ነው።

የአሁኑ ንግግር የዓለም ባንክ የዩክሬንን ኢኮኖሚ ለመደጎም ለዘረጋው መርሀ ግብር የሚሆን 20 ቢሊየን ዶላር ዩናይትድ ስቴትስ ከሰጠች በኃላ የተከናወነ ነው።ገንዘቡ ከቡድን 7 ዲሞክራሲያዊ አገሮች የተገኘ አዲስ ለኪየቭ የሚሰጠው 50 ቢሊዮን ዶላር ብድር አካል ነው ። ገንዘቡ በቡድን ሰባት ሀገራት ውስጥ እንዳይንቀሳቀሱ ከታገዱ ሩሲያ ሉዓላዊ ንብረቶች ከሚገኝ የወለድ ገቢ የሚከፈል ነው።

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ባይደን ለኪየቭ ተጨማሪ የአየር መከላከያ ፣መድፍ ፣ድሮኖች እና የጦር ተሽከርካሪዎችን የሚሆን አዲስ የደህንነት ድጋፍ አፅድቀዋል።ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች ወዲህ ዋሺንግተን ይፋ ያደረገችው 72ኛ ጥቅል ድጋፍ ነው ።

በአውሮፓዊያኑ ጥር 20 ባይደን የአሜሪካ ቀረጥ ከፋዮች ገንዘብ ኪቭን ለመርዳት ውሏል በሚል ወቀሳ ሲያሰሙ ለሰነበቱት ትራምፕ ስልጣን ያስረክባሉ ።ስለ ዕቀዳቸው በዝርዝር ባያስረዱም ፣ ትራምፕ በፍጥነት ጦርነቱን አስቆማለሁ እያሉ ሲናገሩ ተሰምተዋል ።ይህ ንግግራቸው ዩክሬን እጅ እንድትሰጥ የማስገደድ ትርጉም አለው በሚል ብዙ አውሮፓዊያን ያሰጋሉ።

የቡድን 7 ሀገራት መሪዎች የፕሬዚዳንት በሽር አል አሳድን ከስልጣን መውረድ ተከትሎ በሶሪያ ከተካሄደው ወሳኝ የስልጣን ሽግግር ጋር በተያያዙ ፈጣን ሽግግሮች ላይም ትኩረት አድርገዋል።

ሐሙስ ዕለት መሪዎቹ በሶሪያ ውስጥ "ተዓማኒነት ያለው፣ አካታች እና ወደ አንድ ኃይማኖት ወይንም ፖለቲካ እሳቤ ብቻ ያላደላ አስተዳደርን የሚያሰፍን የሽግግር ሂደትን ለመደገፍ ዝግጁ መሆናቸውን በጋራ መግለጫቸው አስታውቀዋል።