በፍጥነት ከተሞችን እየተቆጣጠሩ የመጡት አማጽያን ዋና ከተማዋን ደማስቆን መቆጣጠራቸውን ተከትሎ የሶርያ መንግስት ወድቋል፡፡ ህዝቡም አደባባይ በመውጣት የአሳድ ቤተሰብ የ50 አመታት የበረታ አገዛዝ ማክተሙን አስመልክቶ ደስታውን እየገለጠ ይገኛል፡፡
የሶሪያ መንግስት ቴሌቪዥን ፕሬዚደንት በሽር አላሳድ ከስልጣን መወገዳቸውንና እና ሁሉም እስረኞች ተፈተዋል ሲሉ አማጽያኑ በቡድን ሁነው የሰጡትን የቪዲዮ መግለጫ አቅርቧል።
መግለጫውን ያነበበው ሰው 'ዘኦፕሬሽን ሩም ቱ ኮንከር ደማስቆ' በመባል ከሚታወቀው የተቃዋሚ ቡድን ሲሆን ሁሉም አማፂ ተዋጊዎች እና ዜጎች "የነጻዋ የሶሪያ መንግስት" ተቋማትን እንዲጠብቁ ሲል ጥሪ አቅርቧል።
ይህ መግለጫ የወጣው የሶሪያ ተቃዋሚዎች የጦር አበጋዝ መሪ አሳድ ሀገሪቱን ለቀው ወዳልታወቀ ቦታ መሄዳቸውን ካስታወቁ ከሰዓታት በኋላ ነው፡፡ የሸሹትም በሀገሪቱ ፈጣን የሆነ ግስጋሴን ያደረጉ አማጽያን ደማስቆ ገብተናል ከማለታቸው ቀድመው ነው ተብሏል፡፡
ብዙ የመዲናዋ ነዋሪዎች በሽር አላ አሳድ በሀገሪቱ ላይ ያላቸውን ስልጣን ያጡበትን ፍጥነት ማመን አቅቷቸዋል፡፡ 14 ዓመታት በሚጠጋው የእርስ በርስ ጦርነት፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን የአገሪቱን ግማሽ ሕዝብ የሚሆነውን 23 ሚሊዮን ህዝብም አፈናቅሏል እንዲሁም በርካታ የውጭ ኃይሎችን ጦርነቱን እንዲቀላቀሉ አድርጓል፡፡
የሶሪያው ጠቅላይ ሚኒስትር መሀመድ ጋዚ ጃላሊ መንግስት እጁን ለተቃዋሚዎች ለመዘርጋት እና የሽግግር መንግስት ለመመስረት ዝግጁ ነው ሲሉ በቪዲዮ መግለጫ ተናግረዋል፡፡ በኋላም ለሳዑዲ የቴሌቭዥን ጣቢያ ለአል አረቢያ አሳድ እና የመከላከያ ሚኒስትሩ የት እንዳሉ እንደማያውቁ ተናግረዋል። ቅዳሜ መገባደጃ ላይ ከአሳድ ጋር የነበራቸው ግንኙነት እንደተቋረጠም ገልጸዋል፡፡
አሳድ በጦርነቱ ወቅት እ.ኤ.አ. በ2013 በዋና ከተማው ዳርቻ ላይ የተፈፀመውን የኬሚካል ጦር መሳሪያ ጥቃት ጨምሮ በጦር ወንጀሎች እና በሰብአዊነት ላይ በተፈጸሙ ወንጀሎች ይከሰሳሉ፡፡