እስራኤል ኤምሬትስ ውስጥ የተሰወሩት ረቢ ተገድለው ተገኙ አለች

  • ቪኦኤ ዜና

ዱባይ፣ የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች ውስጥ በሟቹ ረቢ ዝቪ ኮጋን ይተዳደር የነበረው ሪሞን ገበያ- እኤአ ህዳር 24 (ፎቶ አሶሴይትድ ፕሬስ)

በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ውስጥ ደብዛቸው ጠፍቶ ተሰውረው የቆዩት ሞልዶቫዊ እስራኤላዊ የሃይማኖት መምህር (ረቢ) ተገድለው መገኘታቸውን የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ጽህፈት ቤት ዛሬ እሁድ አስታወቀ፡፡
ጽህፈት ቤቱ ባወጣው መግለጫ ድርጊቱ “ዘግናኝ እና ፀረ ሴማዊ የሽብር ክስተት ነው” ብሏል፡፡
ዝቪ ኮጋን የተባሉት የአይሁድ ሀይማኖት መምህር መሰወራቸው የተሰማው ባለፈው ሀሙስ ሲሆን ታግተው ይሆናል የሚል ጥርጣሬ እንደነበር ተሰምቷል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት መግለጫ “የእስራኤል መንግሥት ፍትህ ለመሻት ለግድያው ተጠያቂ በሆኑ ወንጀለኞች ላይ ማናቸውንም መንገድ በመጠቀም እርምጃ ይወስዳል” ብሏል፡፡
የእስራኤል ፕሬዝዳንት አይዛክ ሄርዞግ ግድያውን አውግዘው የኢምሬት ባለሥልጣናት ስለወሰዱት ፈጣን እምርጃ አመስግነዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ አክለውም “ወንጀለኞችን ለህግ ለማቅረብ ያለመታከት ይሰራሉ” የሚል እምነት አለኝ ብለዋል።፡
የኮጋን መሰወር የተሰማው በጥቅምት ወር ኢራን እና እስራኤል የተኩስ ልውውጥ ማድረጋቸውን ተከትሎ ኢራን እስራኤል ላይ የበቀል እርምጃ እንደምትወስድ እየዛተች ባለችበት ወቅት መሆኑ ተመልክቷል።
የእስራኤል መግለጫ ኢራንን ባይጠቅስም የኢራን የስለላ አገልግሎት ከዚህ ቀደም በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ አፈናዎችን መፈጸሙን ጠቅሶ አሶሴይትድ ፕሬስ ዘግቧል።
ምዕራባውያን ባለስልጣናት ኢራን በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ውስጥ የስለላ ስራዎችን እንደምትሠራ እና በመላ ሀገሪቱ የሚኖሩ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢራናውያንን በቅርብ ትከታተላለች ብለው ያምናሉ።
ምንም እንኳን ቴህራን ብታስተባብልም ኢራን እ.ኤ.አ. በ2013 እንግሊዛዊውን ኢራናዊ አባስ ያዝዲን ዱባይ ውስጥ አፍኖ በመግደል ተጠርጥራለች፡፡
እ.ኤ.አ. በ2020 ኢራናዊውን ጀርመናዊ ጃምሺድ ሻርማድን ከዱባይ አግታ ወደ ቴህራን የወሰደች መሆኗም ተነግሯል፡፡
ሻርማድ ባላፈው ጥቅምት ወር ኢራን ውስጥ የሞት ቅጣት ተፈጽሞበታል።