የማኅጸን በር ወይም ግድግዳ ውልቃት ተብሎ በተልምዶ የሚጠራው በኢትዮጵያ በብዛት የማይታወቅ እና ትኩረት ያልተሰጠው ነገር ግን በብዙ እናቶች ላይ የሚከሰት የጤና ችግር ነው።
በእንግሊዘኛ አጠራሩ ፕሮላፕስ ተብሎ የሚጠራውና በሴቷ የመራቢያ አካላት ውስጥ ያሉ ጡንቻዎች በመላላት ወደ ውጭ የሚወጣው የማኅጸን በር ወይም ግድግዳ አብዛኛውን ጊዜ ከወሊድ በኋላ ከባድ ስራ በመስራት፣ ለረጅም ሰዓት በማማጥ፣ በቂ የሆነ ህክምና ካለማግኘት እና በመሳሰሉት ምክንያቶች እንደሚከሰት ባለሞያዎች ይገልጻሉ።
ብዙ ሴቶችም ጉዳዩን አቅልለው በማየት የህክምና አገልግሎት ሳያገኙ ለአመታት ከችግሩ ጋር አብረው እንደሚኖሩ ጥናቶች ያሳያሉ። በዚህ የተነሳም ተደጋጋሚ ለሆነ ኢንፌክሽኖች (የሰውነት መቆጣት)፣ በጊዜ ሂደት የሽንት ማምለጥ፣ እና ይባስ ብሎም እንደማኅጸን ካንሰር ላሉ የከፉ የጤና ችግሮች ተጋላጭ እንደሚሆኑ በተለያየ ጊዜ የተሰሩ ጥናቶች አመላክተዋል።
ኤደን ገረመው በዚህ ችግር ተጠቂ የነበሩ አንዲት እናት፣ የጤና ባለሞያ እና በዚህ ዙሪያ ግንዛቤ ለማስጨበጥ የሚሰራ ተቋምን አነጋግራ ተከታዩን አሰናድታለች።