ሁለት የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅቶች በመንግሥት መታገዳቸውን አስታወቁ

የሕግ ባለሞያዎች ለሰብዓዊ መብቶች ተቋም አርማ

በኢትዮጵያ፣ በሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ዙርያ የሚሠሩ፣ የመብቶችና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል እና የሕግ ባለሞያዎች ለሰብአዊ መብቶች የተባሉ ሁለት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በመንግሥት እግድ እንደተጣለባቸው አስታወቁ።

ድርጅቶቹ ትላንትናና ዛሬ በተናጥል በማኅበራዊ ገጻቸው ላይ ባጋሯቸው መግለጫዎች እንዳስታወቁት፣ እግዱ የተጣለባቸው፣ በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን መሆኑን ገልጸው፣ የእግዱ ምክንያትም፣ “ከዓላማ ውጭ በመንቀሳቀስ የሀገርና የሕዝብ ጥቅምን የሚጎዳ ተግባራት ላይ” ተሰማርታችኋል የሚል መሆኑን አስታውቀዋል።

የሁለቱም ድርጅቶች መግለጫ፣ እንደሚያሳየው፣ የእግዱ ምክንያት "ከፖለቲካ ገለልተኛ መሆን” ሲገባችኹ፣ “ከዓላማው ውጭ በመንቀሳቀስ የሀገርን ጥቅም የሚጎዱ ተግባራት ላይ” ተሠማርታችኋል የሚል ነው፡፡

የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል ወይም ካርድ፣ ትላንትና ባወጣው መግለጫ፣ ኅዳር 3 ቀን 2017 ዓ.ም. ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን በተላከ ደብዳቤ መታገዱን አመልክቶ፣ ለእግዱ የተሰጠው ምክንያት "ከእውነት የራቀ ነው" ብሎታል፡፡

ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ እግዱን ለመጣል የምርመራ ሒደት ማከናወኑን ቢገልጽም፣ ይህ ተግባር ስለመከናወኑ ድርጅታቸው ምንም መረጃ እንደሌለው አስታውቀዋል።

መግለጫው አክሎም “ድርጅታችን ምንም ዓይነት መረጃ የለውም፣ በምርመራው ሂደትም መሳተፍ ይጠበቅብን ነበር” ብሏል። የባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ ውሳኔ “አስፈላጊ የኾኑ ሕጋዊ አካሄዶችን የተከተለ አይደለም” ሲልም ወቅሷል።

ካርድ በመግለጫው፣ “ከዓላማው ውጪ ምንም ዓይነት ተግባራት ላይ እንደማይሳተፍና በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ፍጹም ገለልተኛ ተቋም መኾኑን” አመልክቷል፡፡ "ዴሞክራሲን ብቸኛው የጨዋታው ሕግ ማድረግ" በሚል መሪ ቃሉ እየተመራ፣ በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ማዕቀፍ ውስጥ ለኢትዮጵያ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ተግዳሮቶች መፍትሔ እንዲገኝ” መሟገቱን እንደሚቀጥልም አብራርቷል፡፡ የእግድ ውሳኔው እንዲነሳ፣ ከሚመለከተው የባለሥልጣን መሥሪያ ቤት ጋራ ለመነጋገር ጥረት በማድረግ ላይ እንደኾነም ገልጿል፡፡

በተመሳሳይ፣ የሕግ ባለሙያዎች ለሰብአዊ መብቶች የተሰኘው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት፣ ዛሬ ባወጣው መግለጫ፣ ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ሕዳር 12 ቀን 2017 ዓ.ም. በተጻፈ ደብዳቤ ከማንኛውም የሥራ እንቅስቃሴ የታገደ መሆኑን አመልክቷል፡፡ ድርጅቱ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ከፖለቲካ ነፃና ገለልተኛ ሆኖ በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩ በርካታ ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን ጠቁሟል። ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ ለእግዱ የሰጠው ምክንያት “ማኅበራችንን የማይገልጽና የማይመለከት” ነው ብሎታል፡፡ የተጣለበትን እግድ ለማስነሳትም ሕጋዊ ሂደቶችን ተከትሎ እንደሚንቀሳቀስ አስታውቋል፡፡

የአሜሪካ ድምፅ፣ ስለዚህ ጉዳይ ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን የሥራ ሓላፊዎች፣ ከትላንት ጀምሮ በስልክ እና በአጭር የጹሑፍ መልዕክት አስተያየትና ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡

በተጨማሪም የሁለቱን ድርጅት አመራሮች ለማግኘት ባደረግነው ሙከራ ከወጣው መግለጫ ውጪ ተጨማሪም አስተያየቶችን እንደማይሰጡን ነግረውናል።

ከሁለቱ ድርጅት ሌላ አንድ ተጨማሪ ድርጅት መታገዱን ምንጮቻችን የነገሩን ሲኾን፣ ቪኦኤ ከድርጅቱ መረጃን ለማግኘት ያደረገው ጥረት ባለመሳካቱ የድርጅቱን ስም ከመጥቀስ ተቆጥበናል።