በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ውስጥ ተገድሏል የተባለውን ወጣት በተመለከተ የፌደራልና የክልል መንግሥት ባለሥልጣናት “ኾን ተብሎ የተፈጸመ የጭካኔ ድርጊት" በማለት ከትላንት በስተያ ሐሙስ ዕለት አጥብቀው አውግዘዋል።
የፌደራልና የክልል ባለሥልጣናት ውግዘት የመጣው፣ ሁለት የማሰቃየት እና “አንገት የማረድ” አድራጎት ሲፈጸም ያሳያሉ የተባሉ ያልተረጋገጡ የቪዲዮ ክሊፖች በማኅበራዊ ድህረ ገጾች መሰራጨታቸውን ተከትሎ ነው።
ቪኦኤ ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች ተይዘው የሚታዩ ሁለት የተለያዩ ሰዎችን የሚያሳዩ፣ ሁለት የተለያዩ የቪዲዮ ክሊፖችን ተመልክቷል። ቪኦኤ ሁለቱ የቪዲዮ ክሊፖች፣ መቼና የት እንደተቀረጹ አላረጋገጠም። በመጀመሪያው የቪዲዮ ክሊፕ ግለሰቦቹ በአማርኛ ይናገራሉ። በሁለተኛው ቪዲዮ ላይ በአብዛኛው የሚናገሩት በኦሮመኛ ቋንቋ ነው።
የመጀመሪያው ቪዲዮ አንድ ቢለዋ የያዘ ሰው፣ መሬት ላይ ሌላ ሰው አጋድሞ ይዞ ይታያል። በቀኝ እጁ ቢለዋ የያዘው ሰውዬ፣ መሬት ላይ እንደተጋደመ ምህረት ሲለምን የሚሰማውን የተጎጂውን (የሰለባውን) አንገት ለማረድ ወደ ጉሮሮው ቢለዋውን ይዞ ሲቀርብ ያሳያል። ይኽ ቪኦኤ ያገኘው የ26 ሰከንድ የቪዲዮ ክሊፕ፣ የወጣቱ አንገት ሲታረድ አይታይበትም። ሲታረድ የሚሰማ ድምጽም ኾነ ደም በቪድዮው ላይ አይታይም። በቪዲዮው ላይ የሚታየውን ሰው ማንነት ቪኦኤ ማወቅ አልቻለም። የሰውየው ዕጣ ፈንታ ምን እንደኾነም ቪኦኤ አላረጋጠም።
ቪኦኤ የተመለከተው ሁለተኛው ቪዲዮ፣ አንድ መሬት ላይ በእንጨት የታሰረ ዕድሜው በዐሥራዎቹ የሚገመት አዳጊ በቡድን ሆነው በከበቡት ወንዶች ሲዋከብ ያሳያል። ይኽ የ1 ደቂቃ ከ20 ሰከንድ ቪዲዮ የወጣቱን መገደል አያሳይም። ኾኖም በቪዲዮው ላይ የሚታየው አዳጊ ቤተሰቦች ወጣቱ መገደሉን ተናግረዋል።
በዚህ በሁለተኛው ቪዲዮ ላይ የሚታየው አዳጊ አባት መኾናቸውን ለቪኦኤ የተናገሩት አቶ አማረ አሰፋ፣ ድርጊቱ የተፈጸመው ነሐሴ 22 ቀን 2016 ዓ፡ም በሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ ወሬ ገርቦ ቀበሌ መኾኑን ተናግረዋል።
“ልጄ ደረጀ አማረ የ14 ዓመት አዳጊ ነበር። ከጬካ ከሚባል ደራ ወረዳ ውስጥ ከሚገኝ አካባቢ ወደቤት እየመጣ ነበር። ከዚያም የፋኖ ኃይሎች መንገድ ላይ አግኝተው ወሰዱት። በኋላም ሰለልኩላ የሚባል ከተማ ላይ መገደሉን ሰማን’’ ብለዋል።
በሁለተኛው ቪዲዮ ላይ የሚታየው ተጎጂ ወንድም መኾኑን ለአሜሪካ ድምጽ የገለጸው ክፋይ አማረ፣ ወንድሙ ከሦስት ወራት በፊት ነሐሴ ላይ መገደሉን ተናግሯል። አክሎም “አስከሬኑን ስላላገኘን ልንቀብረው አልቻልንም” ብሏል።
ቪኦኤ ለክፋይ በመጀመሪያው ቪዲዮ ላይ የሚታየውን ወጣት ፎቶ ልኮለት ነበር እና ፎቶው ላይ የሚታየው ወንድሙ አለመኾኑን አረጋግጧል። ወንድሙ በሁለተኛው ቪዲዮ ላይ የታየው ወጣት መኾኑን አረጋግጧል።
በተከታይ ቃለ ምልልስ ፣ አቶ ክፋይ ወንድሙ ተገድሎበታል በተባለው በሰላልኩላ ከተማ ይኖሩ በነበሩ ዘመዶቻቸው አማካይነት የወንድሙን መገደል እንዳረጋገጡ ተናግሯል። ጎረቤቶቹ የወንድሙን መገደል እንደነገሩት ገልጿል። ግድያው እንዴት እንደተፈጸመና የወንድሙ የመጨረሻ ጊዜዎችን አላብራራም። ቪኦኤም በሁለተኛው ቪዲዮ ላይ የሚታየውን ወጣት ዕጣ ፈንታ አላረጋገጠም።
ከማክሰኞ ጀምሮ አንዳንድ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች፣ የፌደራልና በክልል መንግሥታት ድርጊቱን በማውገዝ ቁጣቸውን እየገለጹ ነው።
በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ የዩንቨርስቲ ተማሪዎች ተፈጽሟል የተባለውን ግድያ በማውገዝ ሰላማዊ ሰልፍ አድርገዋል።
ሰልፉን ያደረጉት በአብዛኛው በሰሜን ሸዋ ዞን እየተፈጸመ ነው ያሉትን ግድያ ለማውገዝ መሆኑን የመቱ ዩኒቨርሲቲ እና የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ለቪኦኤ ተናግረዋል።
አንድ የአምቦ ዩንቨርስቲ ተማሪ በበኩሉ እስካሁን ቁጥራቸው በውል የማይታወቁ ተማሪዎች መቁሰላቸውና በእለቱ የመማር ማስተማር ሂደቱም መቋረጡን ተናግሯል።
ሐሙስ ኅዳር 14 ቀን 2017 ዓ.ም ጠዋት ለሠላሳ ደቂቃ ሰልፍ ማካሄዳቸውን ተማሪው ተናግሯል። “በዚህ ሰልፍ ላይ የሰው ልጅ ለምን እንደከብት ይገደላል? ብለነው የጠየቅነው። ከጠዋት 2:30 ላይ ጀምሮ እስከ 3:00 ከተሰለፍን በኋላ በፀጥታ ኃይል ተበተነ። ብዙ ልጆችም ተጎድተዋል።በሆስፒታልና በመኝታ ክፍላቸው ኾነው እየታከሙ የሚገኙ አሉ።” ብሏል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ኮምዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር፣ ለገሰ ቱሉ በማኅበራዊ ገጽ ላይ ድርጊቱን አውግዘው ባሰፈሩት ጹሑፍ፣ "ከሰሞኑ በኦሮሚያ ክልል ሰላሌ -ደራ አካባቢ ጽንፈኛው ቡድን የፈፀመው የአረመኔነት ተግበር ይህንኑ የሚያመለክት ነው። ይህ ፈጽሞ ከሰው ልጅ የማይጠበቅ አፀያፊ ድርጊት መወገዝ አለበት" ብለዋል።
አክለውም "ዓላማቸው በዚህ አሰቃቂ ድርጊት አንዱ ብሔር በሌላኛው ላይ ተነሳስቶ እልቂትና ብጥብጥ እንዲፈጠር ማድረግ ነው። በዚህም እኩይ ፍላጎታቸውን ማሳከት ነው። በዚህ ኢሞራላዊ ድርጊታቸው በህዝብ ዘንድ ፍርሃት በማንገስ ያሻቸውን ማድረግ ነው። ሁለቱም ሞታቸውን ያፋጥነዋል እንጂ የሚሳካ አይደለም።" ብለዋል።
የኦሮሚያ ኮምዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት በቴሌቭዥን በሰጠው መግለጫ በደራ የተፈፀመውን ግድያ አውግዟል። የተባለውን ግድያ የፈፀሙትም የፋኖ ኃይሎችን ናቸው ብሏል።
"የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በጽንፈኛ ሃይሎች የተፈጸመውን የጭካኔ ድርጊት በፅኑ በማውገዝ የዜጎችን ደህንነት ለማረጋገጥ ይሠራል" ብሏል መግለጫው።
የክልላዊ መንግሥቱ መግለጫ የቪዲዮ ምስሎቹን ለይቶ ሳይጠቅስ ፋኖን እና የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊትን “ብሄር የለየ ጥቃት እና በሀገሪቱ ህዝቦች ላይ ግፍ እየፈፀሙ ነው” ሲል አውግዟል።
ከፋኖ ታጣቂዎች ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ በስልክ አለመስራት ምክኒያት ሊሳካልን አልቻለም። ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጥቂዎች ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።
የፌደራል መንግሥትና የኦሮሚያ ክልል ተፈጽሟል የተባለውን ግድያ የሚያሳዩ ቪዲዮዎችን በይፋ አላጋሩም። በተጨማሪም ለትኛው ቪድዮ ቁጣቸውን እየገለጹ እንደኾነ ግልጽ አይደለም።