በአርጀንቲና እግር ኳስ ጉዳይ ፕሬዝዳንቱና ማኅበሩ እየተወዛገቡ ነው

World Cup - South American Qualifiers - Argentina v Bolivia

ማራዶና እና ሊዮኔል ሜሲን የመሳሰሉ የዓለም ኮከብ ተጫዋቾችን ባፈራችውና ሦስት ጊዜ እግር ኳስ ሻምፒዮና የሆነችው አርጀንቲና ፕሬዝዳንት ሃቪየር ሚሌ እና የእግር ኳስ ማኅበሩ ፕሬዚዳንት ክላውዲዮ ታፒያ በቡድኖች አደረጃጀት ጉዳይ እየተወዛገቡ ነው፡፡

የእግር ኳስ ክለቦች የንግድ ድርጅቶችን መልክ ይዘው እንዲዋቀሩ ይፈቅድላቸው ወይስ አይፈቀድላቸው የሚለው ዋነኛው የውዝግቡ መንስኤ መሆኑ ተመልክቷል፡፡

ፕሬዝዳንት ሚሌ ክለቦቹ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ አደረጃጀትን ተከትለው ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ወይም ማኅበር ሆነው በንግድ መልክ እንዲደራጁ ቢፈልጉም የእግር ኳስ ማህበሩ ፕሬዚዳንት አይደግፉትም፡፡

የእግር ኳሱ ፕሬዚዳንት ታፒያ ክለቦች በአባሎቻቸው ባለቤትነት መተዳደራቸውን እንዲቀጥሉ የሚፈልጉ ሲሆን ለአክሲዮን መቅረብም ሆነ ለባለሀብቶች መሸጥ የለባቸውም ባይ ናቸው፡፡

የአርጀቲና ፕሬዝዳንት "የበለጠ ኢንቨትመንት ያመጣል፣ የአሠራር ቅልጥፍናንም ይጨምራል" በሚል ክለቦች በአባሎቻቸው ይሁንታ ወደ ንግድ ድርጅትነት እንዲቀየሩ የሚያስችሉ ህጎችን ቢያወጡም፣ የእግር ኳስ ማህበሩ ግን በዚያ መልኩ የተደራጁ ክለቦችን እንደማይቀበል ከወዲሁ አስታውቋል፡፡ ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን (ፊፋ) እና የደቡብ አሜሪካ የእግር ኳስ ፌደሬሽን የአርጀንቲና መንግሥት በእግር ኳስ ጉዳይ የሚያደርገውን ጣልቃ ገብነት እንደማይቀበሉት በመግለጽ አስጠንቅቀዋል፡፡

ተችዎች የአርጀንቲና እግር ኳስ በሙስና፥ በደካማ አሠራርና ገና ብቅ ያሉ ወጣት ተጫዋቾችን አስቀድሞ በመሸጥ ላይ ያተኮረ ነው ሲሉ ይከሡታል፡፡

የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት እ አ አ እስከ 2028 በኃላፊነት እንዲቀጥሉ የተመረጡ በመሆናቸው ሁኔታውን የበለጠ አስቸጋሪ ማድረጉ ተጠቅሷል፡፡

የአርጀንቲና ፕሬዝዳንት በማኅበሩ አሠራር ላይ ምርመራ እንደሚደረግ የተናገሩ ሲሆን የስፖርት ማህበሩ ከመንግስት የሚያገኛቸው አንዳንድ ጥቅማ ጥቅሞችም እንዲቀነሱ አድርገዋል፡