Your browser doesn’t support HTML5
ባህር ዳር ከተማ ዙሪያ የሚገኘው ጥበበ ጊዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሕክምና ባለሞያዎችና ሠራተኞች በአካባቢው ይገኛሉ ባሏቸው ታጣቂ ዘራፊዎች ይደርስብናል ባሉት ዘረፋና ምክኒያት ሥራ ማቆማቸውን ገለጹ።
የአሜሪካ ድምፅ ያነጋገራቸውና ለደኅንነታቸው ስለሚሰጉ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ሁለት የሕክምና ባለሞያዎች፣ በተለያዩ ጊዜያት የታጠቁ ዘራፊዎች ወደ ሆስፒታሉ ቅጥር ግቢ ዘልቀው በመግባት ሠራተኞቹን በሽጉጥ በማስፈራራት ዘረፋ ማካሄዳቸውን ገልጸው ከሰኞ ኅዳር 9 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ መደበኛ ሥራቸውን እንዳቆሙ ተናግረዋል።
ለደኅንነታቸው በመስጋት ስማቸውን እንዳንጠቅስና ድምጻቸውን እንድንቀይር የጠየቁን አንድ የሆስፒታሉ የጤና ባለሞያ፣ ከአምስት ወራት ወዲህ በተደጋጋሚ የታጠቁ ድንገተኛ ዘራፊዎች ወደ ሆስፒታሉ ቅጥር ግቢ በመግባት ዝርፊያ እንደሚፈፅሙ ገልጸዋል።
ማክሰኞ ኅዳር 3 ቀን 2017 ዓ.ም. የሆስፒታሉን ዳይሬክተር ጨምሮ ሌሎች አምስት ሐኪሞች ግቢው ውስጥ እንደተዘረፉም ተናግረዋል።
የሆስፒታሉ ሠራተኞች ለሚመለከተው አካል ጠንካራ የጸጥታ ኃይል እንዲመደብላቸው በተደጋጋሚ ቢጠይቁም መልስ ማግኘት እንዳልቻሉ ገልጸዋል።
ለተሻለ ሕክምና ከምስራቅ ጎጃም ዞን ቢቸና ወረዳ ታካሚ በበኩላቸው የሕክምና ባለሞያዎቹ አድማ ላይ በመኾናቸው ምክኒያት ፣ ከሰኞ ጀምሮ እስከ ዛሬ አገልግሎት ባለማግኘት እየተጉላሉ መኾኑን በተመሳሳይ የደኅንነት ስጋት ምክኒያት ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ ታካሚ ተናግረዋል።
የጥበበ ጊዮን አጠቃላይ ሆስፒታል በቀን ወደ 3 ሺሕ ታካሚዎችን እንደሚያስተናግድ የሆስፒታሉ አመራሮች ይገልጻሉ። ከዚህ በተጨማሪ በዩንቨርስቲው በሕክምናና ሳይንስ ኮሌጅ የሚማሩ ተማሪዎችም የተግባር ትምሕርት ይወስዱበታል።
በዩንቨርስቲው በሕክምና ሳይንስ ኮሌጅ የአምስተኛ ዓመት ተማሪ መኾኑን የገለጸልንና በደኅንነት ስጋት ምክንያት ስሙ እንዳይጠቀስ ድምጹም እንዲቀየር የጠየቅ አንድ ተማሪ ከሰኞ ጀምሮ የሕክምና ተማሪዎች የተግባር ትምህርት እየወሰዱ እንዳልሆነ ተናግሯል።
“ሆስፒታሉ አጥር የለውም። ጠባቂዎቹም ዱላ ይዘው ነው የሚጠብቁት ሲል ቅሬታውን ያቀረበ አንድ በተመሳሳይ ምክንያት ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ የሕክምና ባለሞያ መደበኛ የፀጥታ ኃይል ካልተመደበ በቀር ሥራ መሥራት አስቸጋሪ እንደኾነ ጠቁሟል።
በባህር ዳር ዩንቨርስቲ በጥበቃ ሥራ የተሰማራና በደኅንነት ስጋት ምክንያት ስሙ እንዳይጠቀስ ድምጹም አየር ላይ እንዳይውል የገለጸልን ግለሰብ፣ የጠበቃ ሥራ የሚሠሩት ያለጦር መሳሪያ በመኾኑ ችግሮች ሲፈጠሩ ምላሽ መስጠት አለመቻላቸውን ገልጿል።
በባህር ዳር ዩንቨርስቲ የጸጥታና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ፣ ኢንስፔክተር ሀብታሙ መለሰ የሆስፒታሉ ሠራተኞች በምሽት በታጠቁ ኃይሎች ዘረፋ እንደሚፈፀምባቸው አረጋግጠዋል። አክለውም፣ በአማራ ክልል ባለፈው ዓመት ከታወጀው አስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ጋራ በተያያዘ ከጸጥታ ኃይሉ ውጭ የጦር መሳሪያ መያዝ የሚከለክል ዐዋጅ በመታወጁ የዩንቨርስቲው ጠባቂዎች የጦር መሳሪያ እንደማይዙ ገልጸዋል። በዚኽም ምክኒያት ወደ ግቢው ታጥቆ የሚመጣውን ማንኛውንም ዘራፊ ለመከላከል አዳጋች እንደሚኾንባቸው ተናግረዋል። ችግሩ ለመፍታትም ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋራ እየተነጋገሩ መኾኑን አስረድተዋል።
ሆስፒታሉን በበላይነት የሚያስተዳድረው ባህር ዳር ዩንቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር መንገሻ አየነ ስለ ጉዳዩ ተጠይቀው በሆስፒታሉ ውስጥ ዝርፊያ መከሰቱን አምነው ፣ዛሬ ጸጥታና ደህንነቱን ከሚመራው ተቋምና ከኮሌጅ ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋራ ተወያይተው ችግሮችን ለመፍታት ውሳኔ ላይ መድረሳቸውን ገልፀዋል።
የጥበበ ጊዮን አጠቃላይ ሆስፒታል በኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ በፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ : በቀድሞው የሱማሊያው ፕሬዝዳንት መሀመድ አብድላሂ መሀመድ " ፋርማጆ "በ2010 ዓ.ም የተመረቀ ትልቅ ሆስፒታል ነው