በተመራጩ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕ ከታጩት ዋና ዋና የካቢኔ ተሿሚዎች መካከል ሁለቱ ከወሲባዊ ውንጀላዎች ጋራ በተያያዙ ውዝግቦች የተጠመዱ መሆናቸው ተመልክቷል፡፡ ትረምፕ ለመከላከያ ሚንስትርነት ያጯቸው የቀድሞው የፎክስ ኒውስ ቴሌቭዥን አቅራቢ ፒት ሄግሴት እና ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ እንዲሆኑ የመረጧቸው የቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት አባል ማት ጌትዝ ከወሲባዊ አድራጎት ውንጀላዎች ጋራ በተያያዙ ውዝግቦች የተጠመዱ ሲኾኑ ሹመታቸው በሕግ መወሰኛው ምክር ቤት መጽደቅ ላይ እክል ሊፈጥር እንደሚችል ተመልክቷል፡፡
ለመከላከያ ሚንስትርነት የታጩት የአርባ አራት ዓመቱ ፒት ሄግሴት እ.አ.አ በ2017 ዓ.ም በወሲባዊ ጥቃት ለወነጀለቻቸው ሴት መጠኑ ያልተገለጸ ገንዘብ መክፈላቸውን በሳምንቱ መጨረሻ ጠበቃቸው ቲም ፓርላቶር ገልጸው መሠረተ ቢስ ያሉት ውንጀላ አደባባይ እንዳይወጣ ለመከላከል መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የአርባ ሁለት ዓመቱ ማት ጌትዝ ደግሞ በተወካዮች ምክር ቤት አባልነት አራተኛቸው የሆነውን የሁለት ዓመት ዘመን እያጠናቀቁ ሳሉ ባለፈው ሳምንት በድንገት ሥራቸውን ለቀዋል፡፡
ጌትዝ ከምክር ቤት አባልነት የለቀቁት ከአስራ ሰባት ዓመት ልጃገረድ ጋራ ወሲባዊ ግንኙነት በመፈጸም እና በድብቅ ሱስ አስያዥ መድሃኒቶች በመውሰድ በቀረቡባቸው ውንጀላዎች ዙሪያ የምክር ቤቱ የሥነ ምግባር ኮሚቴ የከፈተውን ምርምራ ሊያጠናቅቅ ጥቂት ቀናት ሲቀሩት መሆኑ ተመልክቷል፡፡ አንዳንድ የምክር ቤቱ አባላት
ጌትዝ በወሲባዊ ድርጊት በተሰማሩባቸው ሁኒታዎች ራቁት የተነሱ ፎቶዎችን ምክር ቤቱ አዳራሽ ውስጥ ለሰዎች ሲያሳዩ ነበር ብለው ተናግረውባቸዋል፡፡
ጌትዝ ክሱን ያስተባበሉ ሲሆን የፊዴራል መንግሥት ባለሥልጣናትም ክስ እንደማይመሰርቱባቸው በዚሁ ዓመት አስታውቀው እንደነበር አይዘነጋም፡፡
የፒት ሃግሴት ጠበቃ በበኩላቸው ካሊፎርኒያ ውስጥ ከተካሄደ የሪፐብሊካን ፓርቲ የሴቶች ዝግጅት በኋላ በሆቴል ክፍላቸው ከሴቲቱ ጋራ የነበረው ወሲባዊ ግንኙነት የተፈጸመው በሁለቱም ፍላጎት ነው ብለዋል፡፡