ትራምፕ የነዳጅ ኢንዱስትሪ ሥራ አስፈፃሚን ለኃይል መስሪያ ቤቱ ጸሐፊነት መረጡ

ትራምፕ የነዳጅ ኢንዱስትሪ ሥራ አስፈፃሚን ለኃይል መስሪያ ቤቱ ጸሐፊነት መረጡ

በቅርቡ ስልጣን የሚረከቡት ዶናልድ ትራምፕ አዲሱን አስተዳደራቸውን እያዋቀሩ በሚገኙበት በአሁኑ ወቅት ፣ የነዳጅ መስክ አገልግሎት ድርጅት መስራች የሆኑት ክሪስ ራይትን የ ዩናእትድ ስቴትስን የኃይል መስሪያቤት እንዲመሩ መርጠዋል።

የሽግግር ቡድኑ የፕሬዚደንቱን ምርጫ ቅዳሜ ከሰዓት በኃላ ይፋ አድርጓል ። አርብ እለት ትራምፕ ፣ የአገር ውስጥ ጉዳይ መስሪያቤትን እንዲመሩ በመረጧቸው የቀድሞው የሰሜን ዳኮታ ግዛት አስተዳዳሪ ዳግ በርገም የሚመራ አዲስ ብሔራዊ የኃይል ምክር ቤት ይፋ አድርገዋል።

በአዲሱ ኃላፊነታቸው መሰረት በርገም በኃይል ማመንጨት ፍቃድ ፣ምርት ፣ ስርጭት ፣ቁጥጥር እና ማጓጓዝ ላይ የሚሳተፉትን ሁሉንም አስፈፃሚ ቅርንጫፍ ተቋማት የሚያካልል ቡድንን እንደሚመሩ ትራምፕ በመግለጫቸው አስታውቀዋል ። የብሔራዊ ኃይል ምክር ቤት ሊቀመንበር እንደመሆናቸው ፣ በርገም በብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤቱም መቀመጫ እንደሚኖራቸው ተመራጩ ፕሬዝዳንት ተናግረዋል።


ራይት ፣ ኮሎራዶ ላይ መሰረት ያደረገው ፣ ሊበርቲ ኢነርጂ የተሰኘ ኩባንያ ዋና ኃላፊ ቢሆኑም ፣ የፖለቲካ ልምድ ግን የላቸውም ። ነዳጅ ማመንጨትን ጨምሮ ለነዳጅ ዘይት እና ጋዝ ኢንዱስትሪ ተሟጋች በመሆናቸውም ይታወቃሉ። በአውሮፓዊያኑ 2019 ፣ አደገኛ አለመሆኑን ለማሳየት ፈሳሽ ነዳጅ እስከመጠጣት ደርሰዋል ።

በመጋቢት 2024 የአውሮፓዊያኑ ዘመን ይፋ የተደረገው የአሜሪካ ኃይል መረጃ አስተዳደር ሪፖርት እንደሚያሳየው ፣ ሀገሪቱ ላለፉት ስድስት ተከታታይ ዓመታት በማንኛውም ጊዜ ከማንኛውም ሀገር የበለጠ ድፍድፍ ዘይት አምርታለች።


ወርሃዊ የአሜሪካ ድፍድፍ ዘይት ምርት መጠን በአውሮፓዊያኑ ታህሳስ 2023 ከ13.3 ሚሊዮን በርሜል የደረሰ ሲሆን ፣ ይህም በወረሃዊው የምርት መጠን ልኬት ከፍተኛው ሆኖ ተመዝግቧል(AP)።