የቀድሞ የከባድ ሚዛን ሻምፒዮን ማይክ ታይሰን በጃክ ፖል ተሸነፈ 

ትላንት ምሽት በቴክሳስ በተካሄደውና የቀድሞው ታዋቂ ቦክሰኛ ማይክ ታይሰንን በድጋሚ ወደ ቀለበት በመለሰው የከባድ ሚዛን ፍልሚያ ጃክ ፖል በነጥብ አሸናፊ ሁኗል፡፡

የ27 አመቱ የማህበራዊ ሚዲያ ተፅእኖ ፈጣሪ ሽልማት አሸናፊው ፖል እና በ58 አመቱ የቀድሞ የከባድ ሚዛን ሻምፒዮን ታይሰን መካከል የተደረገውን ፍልሚያ በአርሊንግተን በሚገኘው AT&T ስታዲየም በርካታ ተመልካቾች ታድመውበታል፡፡ በኔትፍሊክስም ፍልሚያው በቀጥታ ስርጭት ተላልፏል፡፡

በፍልሚያው ፖል ተፋላሚው ማይክ ታይሰን ላይ 78 ቡጢዎችን ያሳረፈ ሲሆን ታይሰን በበኩሉ 18 ቡጢዎችን ብቻ ተጋጣሚው ላይ ማሳረፍ መቻሉ ተገልጿል፡፤

"በመጀመሪያ ደረጃ ማይክ ታይሰን - እሱ ጋር መፋለም መቻሌ ለእኔ ክብር ነው" ሲል ፖል ከፍልሚያው በኋላ ተናግሯል።

የጉልበት መከላከያ ለብሶ ፍልሚያውን ያደረገው ማይክ ታይሰን ከውድድሩ በኋላ የእግር ጉዳት እንደነበረበት ገልጿል ነገር ግን ለውድድሩ ይህንን ምክንያት ማድረግ አልፈልግም ሲልም ተናግሯል፡፡

በ1980ዎቹ መገባደጃ እና በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ እጅግ አስፈሪ የከባድ ሚዛን ሻምፒዮኖች አንዱ የነበረው ማይክ ታይሰን ይህ በ20 ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ያደረገው ፕሮፌሽናል ፍልሚያ ነው፡፡ ወደ ቀለበቱ እንደገና ይመለስ እንደሆነ ሲጠየቅ ቁርጥ ያለ ምላሽ አልሰጠም።