የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ሃላፊ ለታዳጊ ሃገራት በሚሰጠው የገንዘብ ድጋፍ ዙርያ በኮፕ 29 እየተደረጉ ያሉ ድርድሮች ገና ረጅም መንገድ እንደሚቀራቸው አስጠንቅቀዋል፡፡
በአዘርባጃን ባኩ እየተካሄደ ባለው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ተደራዳሪዎቹ ልዩነታቸው በማጥበብ ከስምምነት ለመድረስ እየተነጋገሩ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በቀጣዩ ሳምንት በጉባኤው ማጠናቀቂያ ላይ ከሚደረገው የሚንስትሮች ስብሰባ አስቀድሞ ከስምምነት ለመድረስ ፍላጎት ቢኖርም በዋና ዋና ጉዳዮች ግን አሁንም ከስምምነት መድርስ አልተቻለም ተብሏል፡፡
የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ሀላፊ ሲሞን ስቲል የዓለማችን ታላላቅ ኢኮኖሚዎች እና ከፍተኛ ብክለትን የሚያስከትሉ የቡድን 20 ሀገራት መሪዎች ሰኞ በብራዚል ሲገናኙ ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጡት ተማጽነዋል።
ለአለም አቀፍ የሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀቶች ተጎጅ የሆኑት አንዳንድ ታዳጊ ሀገራት ከአየር ንብረት ተፅዕኖን ለመቋቋምና ወደ ታዳሽ ሃይል እንዲሸጋገሩ 1.3 ትሪሊዮን ዶላር ዓመታዊ ድጋፍ ጠይቀዋል፡፡
ይህ አሃዝም አሜሪካ፣ የአውሮፓ ህብረት እና ጃፓንን ጨምሮ ለጋሾች ከሚከፍሉት 10 እጥፍ በላይ ነው።