የሴኔት ዲሞክራቶች የፌዴራል ዳኞችን ለመሾም ጥድፊያ ላይ ናቸው 

ፋይል፡ በሴኔቱ የዲሞክራቲክ ፓርቲው መሪ ቻክ ሹመር ንግግር ሲያደርጉ፣ ታኅሣሥ 28 2013 ዓ.ም.

በአሜሪካ የሕግ መወሰኛው ም/ቤት (ሴኔት) አብላጫ ድምጽ ያላቸው ዲሞክራቶች ትረምፕ ሥልጣናቸውን ከመረከባቸው በፊት የፌዴራል ዳኞችን ለመሾም በመጣደፍ ላይ ናቸው።

ባለፈው ሳምንት ምርጫ ውጤት መሰረት ከእ.አ.አ ጥር 3 ቀን 2025 ዓ.ም. ጀምሮ ሪፐብሊካኖቹ ሴኔቱን በበላይነት ከመቆጣጠራቸውና ተመራጩ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕም ሥልጣናቸውን ከመረከባቸው በፊት፣ ዲሞክራቶቹ በፕሬዝደንት ጆ ባይደን የታጩትን 30 የፌዴራል ዳኞች ለመሾም በመረባረብ ላይ ሲኾኑ፣ ምን ያህሉን እጩዎች ማጽደቅ እንደሚችሉ ግን ግልጽ አይደለም ተብሏል።

ሴኔቱ ትላንት በሰጠው ድምጽ 51 ለ 44 በሆነ ውጤት የቀድሞዋ አቃቤ ሕግ ኤፕሪል ፔሪን በኢሊኖይ ግዛት የፌዴራል ዳኛ አድርጎ መርጧል።

ጆ ባይደን ካቀረቡት 30 እጩዎች ውስጥ 16ቱ በሴኔቱ የሕግ ኮሚቴ የተገመገሙ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ 14 እጩዎችም በኮሚቴው ይፈተሻሉ ተብሏል።

የአሜሪካ ሕገ መንግሥት በፕሬዝደንቱ የሚቀርቡትን እጩ የፌዴራል ዳኞች ገምግሞ የማጽደቅ ሥልጣኑን ለሴኔቱ ሰጥቷል። የታቻለውን ያህል ዳኞች እንደሚሾሙ በሴኔቱ የዲሞክራቲክ ፓርቲው መሪ ቻክ ሹመር አስታውቀዋል።

ዶናልድ ትረምፕ በአራት ዓመታት የሥልጣን ዘመናቸው 234 የፌዴራል ዳኞችን የሾሙ ሲኾን፣ በዚህም የፍትህ አካሉን ቀኝ ዘመም እንዲሆን አድርገዋል ተብሏል። በተጨማሪም በጠቅላይ ፍ/ቤቱ የወግ አጥባቂ ዳኞችን በመሾም ስድስት ለሦስት የበላይነት እንዲኖራቸው አድርገዋል።

ባይደን በበኩላቸው በሥልጣን ዘመናቸው 214 ዳኞችን ሴኔቱ እንዲያጸድቅ አድርገዋል። በተጨማሪም ለዘብተኛ የሆኑትን ኬታንጂ ብራውን ጃክሰንን በጠቅላይ ፍ/ቤት ዳኝነት ሾመዋል።