ታላላቅ የዓለም መሪዎች ያልተገኙበት የአየር ንብረት ጉባዔ

የዓለም መሪዎች የተሰባሰቡበት የተመድ የአየር ንብረት ጉባዔ ዛሬማክሰኞ አዘርባይጃን ዋና ከተማ ባኩ ውስጥ ተከፍቷል። ከቀደሙት ጉባዔዎች በተለየ በዘንድሮው ስብሰባ ላይ ያልተገኙ ታላላቅ ሰዎች እና አገሮች አሉ።

ከዚህ ቀደም የተካሄዱት ጉባዔዎች ከዓለም ዋንጫ ውድድር በሚስተካከል ደረጃ ዝነኞች ያሰባሰቡ እንደነበሩ የገለጸው የእሶሲየትድ ፕሬስ ዘገባ በዘንድሮው ጉባዔ የአስራ ሦስቱ ግንባር ቀደም በካይ ካርቦን ዳይክሳይድ አፍላቂ ሀገሮች መሪዎች እንደማይሳተፉ አመልክቷል።

አስራ ሦስቱ ሀገሮች እ አ አ ባለፈው 2023 ዓም ከተለቀቀው የዓለምን አየር የሚያግል በካይ ጋዝ ሰባ ከመቶውን ያፈለቁት መሆናቸውን ዘገባው ጠቁሟል።

የቻይና እና የዩናይትድ ስቴትስ መሪዎች የማይገኙ ሲሆን ህንድ እና ኢንዶኔዢያም መሪዎቻቸውን እንደማይልኩ ተገልጿል።

በመሆኑም ከዓለም 42 ከመቶውን የሕዝብ ብዛት የያዙት አራት ሀገሮች መሪዎች በጉባዔው ላይ ንግግር እንደማያደርጉ ዘገባው ጨምሮ አመልክቷል።