ጋዛ ውስጥ 14 ሰዎች ተገደሉ ፣ ቤይሩት ላይ የአየር ድብደባ ተፈጸመ 

  • ቪኦኤ ዜና

ፍልስጤማውያን በቤቴ ሃኖን ከሚገኙ መጠለያዎች ተፈናቅለው ወደ ሌሎች አካባቢዎች ሲሸሹ፣ ህዳር 3 2017 ዓ.ም. (Photo by Omar AL-QATTAA / AFP)

እስራኤል ጋዛ ውስጥ ባደረሰችው ጥቃት ቢያንስ 14 ሰዎች መገደላቸውን የፍልስጥኤም ባለስልጣናት ተናገሩ።

በተያያዘ ዜና ደቡባዊ ቤይሩት ዳርቻ በሚገኙ የመኖሪያ ሠፈሮች የእስራኤል የአየር ኅይል ጥቃት ማድረሱ ተዘግቧል። ነዋሪዎች እንዳሉት የእስራኤል ኅይሎች ነዋሪዎቹ እንዲወጡ ትዕዛዝ ከሰጡ ግማሽ ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ሰማዩ በጢስ ተሸፍኗል።

ውጊያው የቀጠለ ሲሆን ዓለም አቀፍ የረድዔት ድርጅቶች ባወጡት ሪፖርት እስራኤል ወደ ጋዛ ሰርጥ ተጨማሪ እርዳታ እንዲገባ እንድትፈቅድ በዩናይትድ ስቴትስ የተቀመጠውን የዛሬ ማክሰኞ ቀነ ገደብ አለማክበሯን ተናግረዋል።

የእስራኤል የጦር ኅይል በበኩሉ በጥቃቱ በዋናነት የሚያተኩርበት ወደ ሆነው ወደ ሰሜናዊ ጋዛ ብዙ መቶ የምግብ አቅርቦት ጥቅሎች እና ውሃ እንዲገባ አድርገናል ሲል አስታውቋል።

ባለፈው እ አ አ ጥቅምት ወር የባይደን አስተዳደር እስራኤል ተጨማሪ የምግብ እርዳታ እና ሌላም አቅርቦት ወደጋዛ እንዲገባ እንድትፈቅድ አለዚያ ወታደራዊ እርዳታ ሊቀነስባት እንደሚችል ማስጠንቀቁ ይታወሳል።