ኤርትራ ውስጥ ከ23 ዓመታት በላይ ያለምንም ክስ ታስሮ የሚገኘው እና የስዊድን ዜግነት ያለው ትውልደ ኤርትራዊ ጋዜጠኛ ዳዊት ይስሃቅ፣ ሀሳብን በነጻነት ለመግለፅ መብት ላደረገው ትግል ዛሬ ሰኞ ተሸላሚ ሆኗል።
እ.አ.አ በመስከረም 2001 ዓ.ም የኤርትራ መንግስት ባካሄደው ዘመቻ፣ ከፍተኛ የካቢኔ ሚኒስትሮችን፣ የፓርላማ አባላትን እና ነፃ ጋዜጠኞችን ጨምሮ፣ መንግስት ካሰራቸው ከ24 በላይ ሰዎች መካከል ዳዊት አንዱ ነበር።
ሽልማቱን የሰጠው ኤድልስታም የተሰነው ተቋም ሽልማቱን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፣ ዳዊት 'ኤድልስታም' የተሰኘውን ሽልማት ያገኘው "ሀሳብን በነጻነት ለመግለፅ መብት፣ ለግለሰባዊ እምነት እና ለሰብዓዊ መብት ጥበቃ በመቆም ላደረገው የላቀ አስትዋፅኦ እና ፅናት" መሆኑን አስታውቋል።
አምነትስቲ ኢንተርናሽናል ዳዊትን የህሊና እስረኛ አድርጎ የሚቆጥረው ሲሆን፣ ለፕሬስ ነፃነት የሚሟገተው ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን፣ እሱ እና አብረውት የታሰሩት የስራ ባልደረቦቹ በዓለማችን ለረጅም ጊዜ የታሰሩ ጋዜጠኞች መሆናቸውን አስታውቋል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የመብት ባለሞያዎች በበኩላቸው ኤርትራ በአስቸኳይ ዳውትን ከእስር እንድትፈታ ጠይቋል።
ኤርትራ እስካሁን በዳዊት ዙሪያ መላሽ ሰጥታ የማታውቅ ሲሆን፣ ምናልባትም በህይወት ላይኖር ይችላል የሚል ስጋት አለ። በህይወት ካለ ግን አሁን የ60 አመት እድሜ ይኖረዋል።
ሽልማቱን ሴት ልጁ ቤተልሔም ይስሐቅ ዳዊትን ወክላ በመጪው ሳምንት ስቶክሆልም ውስጥ በሚካሄድ ሥነ ስርዓት ላይ ትቀበላለች።
ዳዊት ከኤርትራ ሸሽቶ ወደ ስዊድን የተሰደደው እ.አ.አ በ1987 ሲሆን፣ የስዊድን ዜግነት ካገኘ በኃላ እ.አ.አ በ2001 በኤርትራ የመጀመሪያ የሆነው የግል ጋዜጣ ሰቲት መሰረተ። ብዙም ሳይቆይ የፖለቲካ ማሻሻያዎችን የሚጠይቁ መጣጥፎች በጋዜጣው መውጣታቸውን ተከትሎ ግን በቁጥጥር ስር ውሏል።